አቡነ ሃብተ ማርያም ጻድቅ

+” አቡነ ሃብተ ማርያም ጻድቅ “+

=>እኒህ ጻድቅ የሃገራችን ኮከበ ገዳም ናቸው:: “ጽድቅና ትሩፋት እንደ ሃብተ ማርያም” እንዲሉ አበው:: ባሕር ከሆነ ጣዕመ ሕይወታቸው ጥቂቱን ለበረከት እንካፈል::

+ጻድቁ መካነ ሙላዳቸው ሽዋ (የራውዕይ) ውስጥ ሲሆን አባታቸው ፍሬ ቡሩክ : እናታቸው ደግሞ ቅድስት ዮስቴና ትባላለች:: በተለይ ቅድስት ዮስቴና እጅግ ደመ ግቡ : ምጽዋትን ወዳጅ : ቡርክት ሴት ነበረች:: እንዲያውም ከጻድቁ መወለድ በፊት መንና ጭው ካለ በርሃ ገብታ ነበር::

+ግን የበቃ ግኁስ አግኝቷት “ከማሕጸንሽ ደግ የሥላሴ ባርያ አለና ተመለሽ” ብሏት እንደ ገና ተመልሳለች:: ጻድቁን ወልዳ አሳድጋም እንደ ገና መንና በተጋድሎ ኑራ 7 አክሊላትን ተቀብላ ዐርፋለች::

+ወደ ጻድቁ ዜና ሕይወት ስንመለስ አቡነ ሃብተ ማርያም ገና ሕጻን እያሉ ከእናታቸው ጋር ቆመው ሲያስቀድሱ “እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ” ሲባል ይሰማሉ:: ይሕችን ጸሎት በሕጻን አንደበታቸው ይዘው ሌሊት ሌሊት እየተነሱ “ማረን እባክህን?” እያሉ ይሰግዱ ነበር::

+የ5 ዓመት ሕጻን እንዲህ ሲያደርግ ማየቱ በእውነት ይደንቃል:: ትንሽ ከፍ ብለው በእረኝነት ሳሉም ፍጹም ተሐራሚና ጸዋሚ ነበሩ:: ጸጋው ስለ በዛላቸውም ልጅ ሆነው ብዙ ተአምራትን ሰርተዋል:: የፈጣሪውን ስም ያቃለውን አንድ እረኛም በዓየር ላይ ሰቅለው አውለውታል::

+ከዚያ ግን ለአካለ መጠን ሲደርሱ ወደ ት/ቤት ገብተው : መጻሕፍትንም አጥንተው መንነዋል:: በአባ መልከ ጼዴቅ እጅ ከመነኮሱ በሁዋላ የሠሩትን ትሩፋትና የነበራቸውን ተጋድሎ ግን የኔ ብጤ ደካማ ሰው ሊዘረዝረው አይችልም::

*ባሕር ውስጥ ሰጥመው 500 ጊዜ ይሰግዳሉ::

*በየቀኑ 4ቱን ወንጌልና 150 መዝሙረ ዳዊትን ይጸልያሉ:: (መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ታላቅ ጸሎት ነው)

*በ40 ቀናት : ቀጥሎም በ80 ቀን አንዴ ብቻ ይመገባሉ::

*ምግባቸው ደግሞ ሣርና ቅጠል ብቻ ነው::

*በየዕለቱ ያለ ማስታጐል ማዕጠንት ያሳርጋሉ:: (ካህን ናቸውና)

*ዘወትር በንጽሕና ቅዱስ ሥጋውን ይበላሉ : ክቡር ደሙን ይጠጣሉ::

*በፍጹም በልባቸው ውስጥ ቂምን : መከፋትን አላሳደሩም::

+በእነዚህና በሌሎች ትሩፋቶቻቸው ደስ የተሰኘ ጌታም ለጻድቁ የእሳትና የብርሃን ሠረገላን ሰጥቷቸው በዚያ እየበረሩ ኢየሩሳሌም ይሔዱ ነበር:: ከብዙ የተጋድሎ ዘመናት በሁዋላም የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ክርስቶስ አዕላፍ መላእክትን አስከተትሎ መጥቶ አላቸው::

“1.ስለ እኔ ረሃብና ጥምን ስለ ታገስክ:
2.ስለ ምናኔሕ:
3.ስለ ተባረከ ምንኩስናህ:
4.ስለ ንጹሕ ድንግልናህ:
5.ቂምና በቀልን ስላለመያዝህ:
6.ስለ ንጹሕ ክህነትህና ማዕጠንትህ:
7.ቅዱስ ወንጌልን በፍቅር ስለ ማንበብህ 7 አክሊላትን እሰጥሃለሁ::”

+”በሰማይም ከመጥምቁ ዮሐንስ ጐን : 500 የእንቁ ምሰሶዎች ያሉበትን አዳራሽ ሰጥቼሃለሁ:: በስምህ የሚለምኑ : በቃል ኪዳንህ የሚማጸኑትንም ሁሉ እንድምርልህ ‘አማንየ! በርእስየ!’ ብዬሃለሁ” አላቸው::

+ቅዱሳን መላእክትም “ሃብተ ማርያም ወንድማችን” ሲሉ አቀፏቸው:: ጌታ ግን በዚያች ሰዓት አንድም ሦስትም ሆኖ ታያቸውና አቅፎ 3 ጊዜ ሳማቸው:: ከፍቅሩ ጽናትም የተነሳ ነፍሳቸው ከሥጋቸው ተለየች:: በዝማሬም ወሰዷት:: {ይህች ቀን (ግንቦት 26) ለጻድቁ ዕለተ ልደታቸው ናት::}

=>አምላከ አበው ወሰማዕት ጣዕመ ፍቅራቸውን: ክብራቸውን: ጸጋ በረከታቸውንም ይክፈለን::

=>+”+ እግዚአብሔር ፍርድን ይወድዳልና::
ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና::
ለዘለዓለምም ይጠብቃቸዋል . . .
ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ::
በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ::
የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል::
አንደበቱም ፍርድን ይናገራል::
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው::
በእርምጃውም አይሰናከልም:: +”+ (መዝ. 36:28-31)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

ምንጭ፡<iframe src=”https://www.facebook.com/plugins/post.php?href=https%3A%2F%2Fwww.facebook.com%2Fyordanos.abebe.54%2Fposts%2F2798760456888527&width=500″ width=”500″ height=”664″ style=”border:none;overflow:hidden” scrolling=”no” frameborder=”0″ allowTransparency=”true” allow=”encrypted-media”></iframe>

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *