#አንተ #አላመሰግንም #ብትል #ዘማሪ #ፍጡር #ፈጠርኩብህ

ቅዱስ ያሬድ ሲታሰብ በሁላችን ኅሊና ውስጥ ወይም በሁላችንም ዕውቀት ውስጥ የሚመጣው ‹‹ዜማ›› የሚለው ቃል ነው፡፡ የቅዱስ ያሬድ ዝርዝር ታሪክና ያበረከተው ሰፊ አስተዋፅኦ በተወሰኑ ካህናትና ምእመናን ቢታወቅም በአብዛኛው ምእመናን ዘንድ ግን ስለቅዱስ ያሬድ ያለን ግንዛቤና መረጃ በጣም ውሱን ነው፡፡ ስለዚህ የቤተ ክርስቲያናችን ብርሃን የሀገራችን ወርቃማ ሀብት ስለሆነው ታላቅ ሊቅ ይመለከተኛል በምንለው በተዋሕዶ ልጆች እንኳን የጠለቀ ግንዛቤ አለመኖሩ ሥራዎቹ ከቤተ ክርስቲያንም አልፎ ለሀገር፣ ከሀገርም አልፎ ለዓለም እንዳይተርፍ አድርጎታል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ለነፍስም ለሥጋም በሰማይ ለሚጠብቀን ሕይወታችንም ሆነ በምድር ላለው ሕይወታችንም የሚሆን ቁስለ ነፍስን የሚያክም አጥንትን የሚያለመልም ድንቅ ድርሰቶችን አበርክቶልናል፡፡

የቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች ከዓለማችን የዜማ ድርሰቶችና ቅኔዎች ልዩ የሚያደርጋቸው እጅግ ብዙ ምክንያቶች ሲኖሩት ዋነኛውና የመጀመሪያው ከተፈጠሩ ጀምሮ ፈጣሪያቸውን ያለማቋረጥና ያለማጓደል ከሚያመሰግኑ መላእክት የተማረው ሰማያዊ ዜማ በመሆኑ ነው፡፡ ይኸውም ‹‹ዋይ ዜማ ዘሰማዕኩ በሰማይ እመላእክት ቅዱሳን እንዘ ይብሉ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር መልዐ ሰማያተ ወምድረ ቅዱሳተ ስብሐቲከ። ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር ሆይ የክብርህ ምስጋና ሰማያትንና ምድርን የመላ ነው እያሉ በሰማይ ከሚኖሩ ከቅዱሳን መላእክት የሰማሁት ዜማ ምን ይረቅ ይም ይጠልቅ እንደምን ያለ ረቂቅ ነው ለዚህ አንክሮ ይገባል።›› በማለት ገልጾልናል፡፡ ስለዚህ ዜማውን እንደ በዓሉ፣ እንደ ወቅቱና እንደ ዕለቱ ሁኔታ እያዛመደና እያዋሐደ ቀምሮታል፡፡

ቅዱስ ያሬድ በምድር ስንኖር ሊኖረን ስለሚገባን ሥነ ምግባርና ማኅበራዊ ትስስር፤ በዚህች ምድር ስለሚያስፈልጉን ነገሮች፤ በዙሪያችን ስላሉ ድንቅ ተፈጥሮዎች ተቀኝቷል፡፡ ለምሳሌ ስለመረጋጋት፣ ስለፍቅርና ስለሰብአዊ እኩልነት ካዜመው ውስጥ ለምሳሌ ቁም በዘሀሎከ ኢታንቀልቅል ወኢትትሐወክ ለዓለመ ዓለም፤ ወዘሰ ሕኑፅ በመሠረተ እግዚአብሔር አልቦቱ ዘተኀጕለ ወኢያፍቱከ ምክሮሙ ለረሲዓን ተዘከር ሠናያተ ዘገብረ ለከ እግዚአብሔር። ወንድሞቼ ሆይ ሰውን መጥላት ምን ይጠቅመናል? ወንድምን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነውና፡፡ ባለህበት ጸንተህ ቁም፤ ተረጋጋ፤ አትነዋወጥ አትጨነቅ፤ ለዘለዓለምም አትታወክ፤ በእግዚአብሔር መሠረት ላይ የታነጸ ሰው ጥፋትና ጉስቁልና የለበትምና፤ የክፎዎች ምክራቸውና ሥራቸው አያስጎምጅህ፤ አንተ ግን እግዚአብሔር በጎ በጎ ነገር ያደረገልህን ብቻ አስብ›› በማለት በኑሮ ሒደት ማኅበራዊ ቀውስ ገጥሟቸው የተጨነቁትን አካላት በዜማው ሲያረጋጋ እናገኘዋለን፡፡

የዝማሬ፣ የፍልስፍና፤ የስነ ከዋክብት፤ የሕግ፤ የታሪክ፣ የመልክዐ ምድርና የቋንቋ ሊቅ የሆነው ቅዱስ ያሬድ ዛሬ ዓለም ለደረሰበት የዜማ፣ የተፈጥሮ ሳይንስና የማኅበራዊ ሕይወት ፍልስፍናም መሠረት ነው ሊያስብል የሚያስችሉ ሰማያዊ ሰነዶችን ትቶልን አልፏል፡፡ የተፈጥሮን ሁኔታ ያስቃኘናል፡፡

ዓለም ‹‹ወርቃማ ሕጎች›› እያለ መጽሐፍ ቅዱስን ወይም ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን መሠረት ያደረጉ፤ እንዲሁም በተለያዩ ዘመናት የተነሡ ደራሲያንን፣ ባለቅኔዎችንና የፖለቲካ ሰዎችን አባባሎች ሲጠቀምበት እናያለን፡፡ ነገር ግን ከዚህ በሰፋ መልኩ ቅዱስ ያሬድ ጆሮ ግቡ በሆኑ ቃላት የተቀመሙ በምሥጢር የተከረከሙ የሰዎችን ሰብእና የሚያክሙ እጅግ ብዙ ‹‹ወርቃማ ሕጎች›› ያሉት ታላቅ ሊቅ ነው፡፡ ለምሳሌ ሰው ደግ በመሆኑ የሚያገኘውን ጥቅም ሲናገር
‹‹ኅድግዋ ለእኪት ወዴግንዋ ለሠናይት እስመ ሠናይ ምክር ባቲ። ተገሀሥ እምእኩይ ወግበር ሠናየ ወኢትሑር በምክረ ረሲዓን ብፁዕ ውእቱ በአፉሁ ዘኢተናገረ ከንቶ ይጹም ዐይን ይጹም ልሳን ዕዝንኒ ይጹም እምሰሚዐ ኅሡም በተላሕዮ። ክፋትን ተዋት፤ ደግነትን ተከተላት፤ ደግነት መልካም ምክር አለባትና፤ ከክፉ ሽሽ መልካም አድርግ፤ በክፉዎች ጎዳና አትሂድ። በአንደበቱ ያልሸነገለ፤ ከንቱን ነገር ያልተናገረ ብፁዕ ነው፤ ዐይን ክፉ ከማየት፤ አንደበት ክፉ ከመናገር፤ ጆሮ ክፉ ከመስማት ይጹም›› በማለት ተቀኝቷል፡፡

ቅዱስ ያሬድ ኢትዮጵያ ከዘመናት በፊት ለዜማና ለትያትር መነሻ መሆኗን የሚያበሥር አዲስ የጥናትና የምርምር በር ከፍቷል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ነገረ መለኮትን፣ የሰውን ተፈጥሮና በዓለማችን ያሉ ፍጥረታትን በምሥጢር እያመሣጠረ አንድነታቸውንና ልዩነታቸውን በተለያየ ኅብረ ምሥጢር ገልጿል፡፡ ‹‹ሰዎች በሥርዓት ሊኖሩ ይገባል›› የሚለውን አምላካዊ ቃል መሠረት አድርጎ ስለ ሥነ ምግባር ያላነሣው ርእሰ ጉዳይ የለም፤ ከቅዱስ ያሬድ የዝማሬ መጻሕፍት ድርሰቶች በጥልቅ ፍልስፍና ላይ የተመሠረቱ በመሆናቸው ሰፊ የማኅበራዊ ሳይንስ ትንተናዎች እንዳላቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ይገልጻሉ፡፡ ለረጅም ዘመናት ለሀገራችን ብሎም ለዓለማችን የዜማና የድራማ ጥበብ መነሻ የማኅበራዊ ሕይወት ፍልስፍናዎቹ ለከፍተኛ ምርምርና ጥናት ግብዓት እንዲሆኑ በማድረግ ዓለም አቀፋዊ ውይይቶችና ንግግሮች እንዲፈጠሩበት የሚያደርግ በመሆኑ ሀገራዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ የራሱን ድርሰት ጽፎ ለጽሑፍ ሥራዎች የመጀመሪያ ፈር ቀዳጅ መሆን እንዲሁም የብራና የጽሑፍ ሥራ ይበልጥ እንዲጠናከር በማድረግ ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ መስፋፋትና ዕድገት ትልቁን ሚና አበርክቷል፡፡

ቅዱስ ያሬድን ድንቅና ልዩ ከሚያሰኙት ምክንያቶች አንዱ በዓለማችን የመጀመሪያው የዜማ ምልክቶች (Musical Notation) ደራሲ በመሆኑ ነው፡፡ ዜማን ቅርጽ በማስያዝ ሳይጠፋ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ያደረገ ለሌሎች የዜማ ሊቃውንት ፈር የቀደደ ሊቅ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ገና የ፲፪ ዓመት ልጅ እያለ በተፈጥሮዋ ትንሽ ከምትባለው ትል የጽናትን ውጤት ተገንዝቦ የሰው ልጅ እየወደቀና እየተነሣ ለውጤት መትጋት እንዳለበት እንዲሁም የሕይወት ስኬት የብዙ ልፋቶች ውጤት እንደሆነ በማመን ተስፋ ባለመቁረጥ በትዕግሥትና በጽናት ፍሬ ለማፍራት መታገል እንደሚገባው ተምሮ ያስተማረ ሊቅ ነው፡፡ ለዜማ ጥበባት ማኅፀን የሆነው መተኪያ የማይገኝለት ያሬዳዊ ዜማ ለኢትዮጵያ ውበቷ፤ የኩራት መቀነቷ ነው፤ መንዝራ የማትጨርሰው ከየዘመኑ ጋር አብሮ የሚጓዝ ሀብቷ ነው፡፡

የቅዱስ ያሬድ የዜማ ድርሰቶቹ የተዘጋጁበት የብራና መጻሕፍት፣ የተደጎሱበት ሁኔታና የተለበዱበት ቁሳቁስ እጅግ የረቀቀ ፈጠራ የሚታይበት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በዝማሜ፣ በወረብ፣ በሽብሸባና በጸናጽል የሚቀርቡት የዜማ ድርሰቶቹ ምን ያህል እይታን እንደሚማርክ፣ ጆሮን እንደሚስብና ቀልብን እንደሚገዛ ለማየት ከተለያዩ ዓለማት ተሰባስበው በሚመጡ ዜጎች የሚታጀበውን እንደ መስቀል፣ ጥምቀት ያሉ በዓላትን ማስታወስ በቂ ነው፡፡ ዛሬ በቅርስነት በተባበሩት መንግሥታት /UNESCO/ የተመዘገበው የመስቀል በዓል ከቅዱስ ያሬድ ዝማሬዎች ውጪ ስናስበው ራቁቱን መሆኑን እናያለን፡፡

ስለዚህ ለእነዚህ በዓላቶቻችን ውበትና ድምቀት ጌጥና መሠረት የሆነውን ሊቅ የኖረባቸውን መካናት፤ ወንበር ዘርግቶ ያስተማረባቸውን ስፍራዎች፤ ለድርሰቶቹ የተጠቀመባቸውንና የተገለገለባቸውን ቁሳቁሶች የቱሪስት መዳረሻና መስህብ እንዲሆኑ በመፍጠር ማሳደግ ስልጡንነት መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡ እነዚህ የቅዱስ ያሬድ የጸጋ ትሩፋቶች የበለጠ እንዲዘከሩ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠር አለባቸው፡፡

ዛሬ በሰለጠኑ ሀገሮች የነበሩ ፈላስፎች ሥራዎቻቸውን በዓለም መድረክ ስላስተዋወቁላቸው መካነ መቃብሮቻቸውና ይገለገሉበት የነበረው ቁሳቁስ ሳይቀር እየተጎበኙ ለሀገራቸው በሕይወት እያሉ ካበረከቱት ጥቅም በላይ ከሞቱ በኋላ ያበረከቱት ጥቅምና አገልግሎት እየበለጠ ሄዷል፡፡ በዚህ መልኩ የሰለጠኑ ሀገሮች የቱሪስቶቻቸውን ፍሰት ከጨመሩበት መንገዱች አንዱ የሊቃውንቶቻቸውን ታሪክ ማስተዋወቅ ነው፡፡

ቅዱስ ያሬድ በመንፈስ ቅዱስ ቃኝነት ያበረከተልን በዓለም ተወዳዳሪ የሌለውን ይህን ዜማ በከፍተኛ ተጋድሎ ጠብቀው ከትውልድ ወደ ትውልድ በማስተላለፍ እስካሁን ላደረሱልን የኢትዮጵያ ሊቃውንት አባቶቻችን ከፍተኛ የሆነ አድናቆትና ምስጋና ሊሰጣቸው ይገባል፤ የአሁኑ ትውልድም ለዘመናት ተጠብቆ የኖረውን ዜማና ባህል ዘመኑ በሚጠይቀው ሁኔታ ተንከባክቦ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ይጠበቅበታል።

ሊቀ ጉባኤ ጌታሁን ደምፀ
ኆኅተ ስብከት ዘቅዱስ ቅጽ አንድ