የበገና ታሪካዊ አጀማመር

የበገና ታሪካዊ አጀማመር
በገና በተወጠሩ ክሮች የሚሰራ የኢትዮጵያ ጥንታዊ የዜማ መሳሪያ ነው። በገና ሌላው ስሙ በግዕዝ እንዚራ ተብሎ ይጠራል። ቁመቱ ረዘም ገበታው ሰፋ ያለ ከ 90 ሳንቲ ሜትር እስከ 140 ሳንቲ ሜትር ርዝመት ያለውና 10 ጅማቶች (አውታሮች) ያሉት ጥንታዊ የኢትዮጵያ የባህል የሙዚቃ መሳርያ ነው።
“በገና”፡- እንደሌሎች የሃገራችን ጥልቅ ብሔራዊ የታሪክ ሃብቶችና በታሪክም ከእስራኤል ቀጥሎ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ብቸኛ ጥንታዊ የዜማ መሣርያ ጥንታዊ ይዘቱን የጠበቀ የሀገር ሀብት እንደ መሆኑ መጠን ሁለት ዓይነት ትርጉም አለው፡፡
እነርሱም፡-
1. ሰዋስዋዊ ትርጉምና
2. ሥነ ቃላዊ ትርጉም………….. ይባላሉ፡፡
1. የበገና ሰዋስዋዊ ትርጉም፡- “በገና” የሚለው ስምና “በገነ” የሚለው ግሥ በተለያዩ መዝገበ ቃላትና የቋንቋ ሊቃውንት ተተርጉሞ እናገኛለን፡፡
ለምሳሌ፡-
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ “መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ መዝገበ ቃላት ሐዲስ” በሚል መጽሐፋቸው በሁለት መልኩ ማለት “ሲጠብቅና ሲላላ” ብለው በማመሳጠር እንዲህ ብለው ተርጉመውታል፡፡ በገና፡- በዕብራይስጥ ናጌን ይባላል ካሉ በኋላ ሲተረጉሙት
፡- ነዘረ፣ መታ፣ ደረደረ፣ ማለት ነው፡፡ ሲጠብቅ ግን ፡- ነደደ፣ ተቆጣ… ያሰኛል ብሏል፡፡
በገና፡- በቁሙ መዝሙር ማለት ነው ብለውም ፈትተውታል፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልደ ክፍሌ፡ መጽሐፈ ስዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ) አባ ዮሐንስ ገ/እግዚአብሔር የትግርኛ መዝገበ ቃላት በተባለ መጽሐፋቸው፡- በገናን በቁሙ በገና ብለው ተርጉመውታል፡፡ (አባ ዮሐንስ
ገ/እግዚአብሔር፣ ትግርኛ አማርኛ መዝገበ ቃላት፣ 1948፣ አሥመራ) ከሳቴ ብርሃን ተሰማ “የአማርኛ መዝገበ ቃላት” በተሰኘ
መጽሐፋቸው እንዲህ ዓይነት ትርጉም ሰጥተውታል፡፡
– በገና፡- በአሥር አዉታር ጅማት በገናን ሠራ፣ ቃኘ፣ ደረደረ፣ ድምጽን እያጣራ፣ እያጣቀሰ፣ እየነዘረ… በገናን በገነ… ካሉ በኋላ
– በገነኛ፡- የሚለው ደግሞ በገናን የሚመታ፣ በገናን የሚያውቅ ደርዳሪ… ማለት ነው ብለው ተርጉመውታል፡፡ (ከሳቴ ብርሃን ተሰማ፣ የአማርኛ መዝገበ ቃላት፣ 1951 ዓ.ም፣ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፣ አዲስ አበባ)
2. የበገና ሥነ ቃላዊ ትርጉም፡- በገነ፡- አደረቀ፣ አቃጠለ፣ አነደደ… ማለት ነው፡፡ በገናም ከዚህ የሚወጣ ስም ነው፡፡ የዚህ ትርጉም ማግኘት ዋና ምክንያትም ሁሉም ነገር (የበገና ሁለገብ ሰውነት) በደረቅ ነገሮች ማለትም በደረቅ እንጨትና በደረቅ ቆዳ እንዲሁም በደረቅ ጅማት የሚሠራ ወይም የሚዘጋጅ ስለሆነ በገና ተባለ ተብሎ ይተረጐማል፡፡ በገና፡- “በ” እና “ገና” በመነጣጠል የሚያስገኘው
ትርጉም በመጠቀም… በ … ገና…. በገና በዓል ወይ በገና ወቅት የሚደረደር የምስጋና መሣርያ ስለሆነ በገና ተባለ ተብሎ ይተረጎማል፡፡
በገና፡- በገነ ማለት ደረደረ ማለት ነው፡፡ ስለሆነም በገና ማለት ድርደራ፣ ምስጋና፣ መዝሙር… ማለት ነው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃ መሠረት በማድረግ ይተረጎማል፡፡
ለምሳሌ፡-
o “አቤቱ አምላኬ በበገና አመሰግናለሁ” መዝ.42/43፡4
o “ለእግዚኣብሔር በገና ደርድሩለት” መዝ.48፡5
o “እግዚኣብሔርን በመሰንቆ አመስግኑት አሥር አውታር
ባለው በበገና ዘምሩለት” መዝ.32/33፡2
የዚህ አጭር ጥናታዊ ጽሑፍ ኣቅራቢ ግን ከሁለቱም ወገን በሚወሰዱ የትርጉም መመሳሰል በመነሳት በምስጢር ከበገና መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ጋር የተሻለ ቀረቤታ ያለውን ትርጉም ቢሆን ይመርጣል፡፡ በመሆኑም፡-
በገነ፡- ደረደረ፣ መታ፣ አነዘረ…. ወዘተ ማለት ነው በሚለው መልካም ትርጉም ይስማማል፡፡ ምክንያቱም ከነባራዊ የበገና ማኅበራዊም ሆነ መንፈሳዊ እሴት ማለትም ከድርጊቱ ወይም ከአቀራረቡ (ከአገልግሎቱ) ጋር አብሮ ይሄዳልና ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት፡-
በገና፡- ማለት ድርደራ፣ ምስጋና፣ መዝሙር… ወዘተ ማለት ነው፡፡ በገነኛው ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ በገናን
ሲተረጉም መዝሙር፣ ምስጋና… በማለት ሲገልጽ እናገኘዋለንና፡፡
የበገና አሰራር
ሳጥኑ፣ ምሰሶዎቹ፣ ብርኩማውና ቀምበሩ ከንጨት የሚሰሩ ናቸው። አውታሮቹም ከጅማት ይሰራሉ። ሳጥኑ በበግ ወይም በከብት ቆዳ ይሸፈናል። ድዝና ጥዝ እንዲል 10 ቁርጥራጭ ቆዳዎች በብርኩማውና በአውታሮቹ መካከል ይስተካከላሉ። ቀምበሩ የእግዚአብሔር ምሳሌ (ምልክት) ነው። ምሰሶዎቹ በስተቀኝ የቅዱስ ሚካኢል በስተግራ የቅዱስ ገብርኢል ምሳሌዎች (ምልክቶች) ናቸው። ጅማቶቹ (አስሩ አውታሮች) የአስርቱ ቃላት ኦሪት ምሳሌ (ምልክት) ናቸው። የድምጽ ሳጥኑ (ገበታው) የእመቤታችን የድንግል ማርያም ምሳሌ ነው። ብርኩማው የሙሴ አስርቱን ትዕዛዛት የተቀበለበት የደብረ ሲና/የሲና ተራራ ምሳሌ ነው።
የበገና ታሪካዊ አጀማመር፡-
በገና፡- በትክክል መቼና እንዴት ተጀመረ የሚለው ጥያቄ መልሱ ከባድ ቢሆንም ሁላችንም እንደምናውቀው፣ ዓለምም ቢሆን በስፋት በግልጽ በአደባባይ እያወደሰው እንዳለ የሁሉም ጥበባት ማለትም ሥጋዊ ጥበብንም ጨምሮ መገኛቸው ወይም ምንጫቸው መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ በመሆኑም nበመጽሐፍ ቅዱስ ለመጀመሪያ ጊዜ ተገልጾ የምናገኘው የምስጋና ወይም የዜማ መሣሪያ በገና ብቻ ነው፡፡
እንደ መጽሐፍ ቅዱስ እውነታ የመረመርነው እንደ ሆነ፡- በገና ለመጀመሪያ ጊዜ የደረደሩት የላሜህ ልጅ የዩባል / ኢዮቤል/ ልጆች ነበሩ (ዘፍ.4፡19-24)፡፡ ይኸውም ዓይነ ስውር (ማየት የተሳነው) የነበረ ላሜህ አያታቸው በበረሃ እየሄደ እያለ ቃኤል ተቅበዝባዥ ነበርና ለብቻው በዱር ተሰውሮ ሲንኮሻኮሽ ሰምቶ መንገድ ይመራው ለነበረው ረድእ (መንገድ መሪ) “እጄ ይሞቅብኛል፣ ቅጠሎች ሲንኮሻኮሹም እሰማለሁ አራዊት መጥቶብናል መሰለኝና ድንጋይ አቀብለኝ” ካለው በኋላ ድንጋዩን ተቀብሎ በተሰማው አቅጣጫ ቢወረውር ግንባሩን መትቶ ገደለው፡፡
ቀርበው ሲመለከቱት ቃየን ሆኖ ሲያገኘው እጅግ መሪር የሆነ ለቅሶ አለቀሰ፡፡
ላሜሕ ወደ ቤቱ ተመልሶም ዓዳና ሴላ ለሚባሉት ሚስቶቹ “ስምዓኒ ዓዳ ወሴላ አንስትያየ አነ ቀተልክዎ ለቃየን አቡየ፡- ዓዳና ሴላ ሚስቶቼ ሆይ ስሙኝ፤ እኔ ዛሬ አባቴ ቃየንን ገድየዋለሁና…” በማለት ነገራቸው፡፡ እነርሱም የሆነውን ሁሉ ታሪካዊ ተዋረዱን ጠብቀው የታሪክ
እውነታውን ለልጆቻቸው ተናግረዋል፡፡ በዚህም የላሜህ የልጅ ልጆች (የዩባል ልጆች) በቃየን ሞት ብቻ ሳይሆን በወላጆቻቸው የአሟሟት ሁኔታ እጅግ አዘኑ፡፡ ይኸውም አቤል በቅንዓት ምክንያት በገዛ ወንድሙ በቃኤል መገደሉ፤ ቃየንም “ተባርዮን የማያስቀር አምላክ ነውና” በገደለው ዓይነት የአገዳደል ዘይቤ (“ሰይፍ ሚያነሱ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና” ማቴ.26፡52፤ እንዲል) በድንጋይ በአምስተኛ ልጁ በላሜሕ መሞቱ… እያወጡ እያወረዱ እጅግ ከማዘናቸው የተነሳ በገና ለመጀመርያ ጊዜ ከደረቁ ቁሳቁሶች አበጅተው በመሥራት በበገና እያንጎራጎሩ ሐዘናቸውን ገልጸዋል፡፡
በዚህም በገና ከፍጥረተ ዓለም ብዙም ባልራቀ ሁኔታ (ከአዳም ዘጠነኛ የትውልድ ሐረግ በሆኑ አበው) የተገኘ የመጀመርያ የሐዘን፣ የእንጉርጉሮ፣ የንስሐ፣ የልመናና የምስጋና መሣሪያ ነው እንላለን፡፡ ተዋረዱም፤
አዳም፡- ቃኤልን ይወልዳል
ቃኤል፡- ሄኖሕ ይወልዳል
ሄኖሕ፡- ጋይዳድ ይወልዳል
ጋይዳድ፡- ሜኤል ይወልዳል
ሜኤል፡- ሙቱሣኤል ይወልዳል
ማቱሣኤል፡- ላሜሕ
ላሜሕ፡- በገና የሚደረድሩትን አባት ይወልዳል (ስማቸው በመጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ አልተገለጸም)፡፡ በመሆኑም ከአዳም ዘጠነኛ ትውልድ የሆኑ የላሜሕ የልጅ ልጆች በሆኑት በእነዚህ አበው ምክንያት በገናን ተዘጋጅቶ መደርደር ተጀመረ፡፡
ቃለ በገና፡- ቃለ ማኅዘኒ
፡- ድምፀ ማኅዘኒ … ነው፡፡
ምክንያቱም በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት አራቅቀው እንደሚተረጉሙት ይህ ምድራዊ ማኅዘኒ ዜማ የመጣው በዮባል ልጆች ኃዘንና እንጉርጉሮ ምክንያት እንደሆነ ይኸው ከላይ የተጠቀሰው ታሪክ ጠቅሰው ያትታሉ፣ ያመሰጥራሉ፡፡ ይኸውም ከላይ እንደተገለጸው፡-
o ቃየል ወንድሙ አቤልን መግደሉ፤
o ቃየል ደግሞ በልጁ በላሜህ መገደሉን፤ እያስታወሱ የዩባል ልጆች የደረቀ እንጨት ጠርበውና አለዝበው፣ ቆዳ ወጥረው፣ ፍቀው፣ አድርቀውና ዳምጠው፣ ጅማት አክርረውና አበግነው… በቃለ ማኅዘኒ፣ በድምፀ ማኅዘኒ… ያንጐራጉሩ ነበር በማለት ሊቃውንቶቻችን
ያትታሉ፡፡ በዚህ ታሪካዊ እውነታ ምክንያት ነው “በገና” ቃለ ማኅዘኒ፣ ድምጸ ማኅዘኒ ሆኖ የሐዘን ማለትም የንስሐ፣ የልመናና
የምስጋና ማቅረቢያ የዜማ መሣሪያ በመሆን አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው፡፡ የበገና የአጀማመሩ ታሪክ በዩባል ልጆች ቢሆንም ዘመናት አልፎ ከትውልድ ትውልድ ሲተካ ይዘቱም ሆነ ዓይነቱ እየተሸሻለ መጥቶ የበገና አጠቃላይ ማኅበራዊ ሚናውም ሆነ መንፈሳዊ አገልግሎት ይበልጥ ጎልቶ የታወቀው ግን በመዝሙረኛው (በበገነኛው) በቅዱስ ዳዊት ምክንያት ነው፡ ፡
በገና ወደ ሀገራችን እንዴት መጣ?
በገና ወደ ኢትዮጵያ የገባው ከክርስቶስ ልደት በፊት በቀደምት የኢትዮጵያ ነገስታት በኩል ሲሆን በቅርብም ከነበሩ ነገስታት አጼ ምኒልክና አጼ ቴዎድሮስ በገና ይደረድሩ እንደ ነበር ይነገራል። በሌላ በኩል ደግሞ
የበገና ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ የአመጣጥ ታሪክ ሁለት ዓይነት አመለካከቶች አሉ፡፡
1. የሀገራችን ኢትዮጵያ የሥልጣኔዋ ውጤትና በሕገ ልቡና የማመንዋ ውጤት ነው፡፡ /የተጀመረ እዚሁ ሀገራችን ነው የሚል ታሪካዊ አንድምታ ነው፡፡/
2. በቀዳማዊ ምኒሊክ ጊዜ ከታቦተ ጽዮን ጋራ አብረው ከመጡት የዜማና የሥርዓተ አምልኮ ንዋያተ ቅድሳት፣ መጻሕፍት… ወዘተ አንድ ሆኖ የመጣ ነው የሚሉ ሲሆን ይህንኑ አመለካከትም ይበልጥ በሀገራችን ጠበብት ሊቃውንት በስፋት ይተረጎማል፣ ይተረካል… ይታመናልም፡፡
የበገና አገልግሎት፤
በገና የሚያገለግለው ለመንፈሳዊ ትሩፋት ማለትም ለምስጋናና ለልመና ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም ተመርጦ ለቤተ መቅደስ አገልግሎት ብቻ ይውላል፡፡ ለምሳሌ፡-
“አቤቱ አምላኬ በበገና አመሰግንሀለሁ” መዝ.42/43/4
“አሥር አውታርም ባለው በበገና ዘምሩለት”
መዝ.32/33/2
“ለእግዚአብሔር በገና ደርድሩለት” መዝ.4.8/5/… ወዘተ ከተመዘገቡት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃዎች ጥቂቶቹ
ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እንደአስፈላጊነቱ ለማኅበራዊ እሴት፣ ለሃገር ክብር፣ ለሉዓላዊነት… በገና ይደረደራል፡፡ ለዚህ ጥሩ ማስረጃችን በአፄ ቴዎድሮስ ጊዜ የተደረደረውና እስከ አሁን ድረስ የበገና መማርያ የሆነው የበገና አገልግሎት
ነው፡፡ ከዚህ ውጭ በገና ለዓለማዊ ፍላጐት ማስፈጸሚያ ማለትም፡- ለዳንስና ለዳንኪራ፣ ለዘፈንና ለጭፈራ፣ ለዝናና ለጉራ ለቀልድና ለፉከራ … ወዘተ ፈጽሞ አገልግሎት አይሰጥም፡፡
የበገና ዜማ በአብዛኛው ለፈጣሪያችን ምስጋና ፀሎት ለማቅረብና ባጫጭር ዜማዎች የዚህ አለም አላፊነትን የሚናገር ሰዎችን ለበጎ ሥራ የሚቀሰቅስ ወደ ንስሐ የሚጠራ ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሚጠቅም ነው።
የበገና ጥቅም፡-
ከላይ እንደተገለጸው በገና በዋናነት ለመለኮታዊ የእግዚአብሔር ፈቃድ ማስፈጸሚያ ማለትም ለምስጋናና ለልመና የሚያገለግል ሲሆን በተጨማሪም ለማኅበራዊ እሴት መግለጫ የሚውል መንፈሳዊና ጥንታዊ የዜማ መሣሪያ ነው፡፡
ለምሳሌ፡-
እግዚአብሔርን ለማመስገን እና እግዚአብሔርን ለመለመን ስለ በገና በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፉ በአብዛኞቹ የሚገልጹት “በገና ለምስጋናና ለልመና ሲቀርብ” በመሆኑ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ማውጫ ያገኘኋቸው እነሆ፡፡
ኦሪት ዘፍጥረት 4፥21 የወንድሙም ስም ዩባል ነበረ እርሱም በገናንና መለከትን ለሚይዙ አባት ነበረ። 31፥27 ስለምን በስውር ሸሸህ? ከእኔም ከድተህ ስለምን ኮበለልህ? በደስታና በዘፈን በከበሮና በበገና እንድሰድድህ ለምን አልነገርኸኝም? መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ
10፥5 ከዚያም በኋላ የፍልስጥኤማውያን ጭፍራ ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ኮረብታ ትመጣለህ ወደዚያም ወደ ከተማይቱ በደረስህ ጊዜ፥ በገናና ከበሮ እምቢልታና መሰንቆ ይዘው ትንቢት እየተናገሩ ከኮረብታው መስገጃ የሚወርዱ የነቢያት ጉባኤ ያገኙሃል።
16፥16 በገና መልካም አድርጎ የሚመታ ሰው ይሹ ዘንድጌታችን በፊቱ የሚቆሙትን ባሪያዎቹን ይዘዝ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ክፉ መንፈስ በሆነብህ ጊዜ በእጁ ሲመታ አንተ ደኅና ትሆናለህ አሉት። 16፥17 ሳኦልም ባሪያዎቹን፦ መልካም አድርጎ በገና መምታት የሚችል ሰው ፈልጋችሁ አምጡልኝ አላቸው። 16፥18 ከብላቴኖቹም አንዱ መልሶ፦ እነሆ፥ መልካም አድርጎ በገና የሚመታ የቤተ ልሔማዊውን የእሴይን ልጅ አይቻለሁ እርሱም ጽኑዕ ኃያል ነው፥ በነገርም ብልህ፥ መልኩም ያማረ ነው፥ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነው አለ።
16፥23 እንዲህም ሆነ ከእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ መንፈስ
በሳኦል ላይ በሆነ ጊዜ ዳዊት በገና ይዞ በእጁ ይመታ
ነበር ሳኦልንም ደስ ያሰኘው ያሳርፈውም ነበር፥ ክፉ
መንፈስም ከእርሱ ይርቅ ነበር።
18፥10 በነጋውም ሳኦልን ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር
ዘንድ ያዘው፥ በቤቱም ውስጥ ትንቢት ተናገረ። ዳዊትም
በየቀኑ ያደርግ እንደ ነበረ በእጁ በገና ይመታ ነበር።
ሳኦልም ጦሩን በእጁ ይዞ ነበር።
19፥9 ሳኦልም ጦሩን ይዞ በቤቱ ተቀምጦ ሳለ ክፉ
መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያዘው። ዳዊትም በእጁ
በገና ይመታ ነበር።
መጽሐፈ ሳሙኤል ካልዕ
6፥5 ዳዊትና የእስራኤልም ቤት ሁሉ በቅኔና በበገና
በመሰንቆም በከበሮም በነጋሪትና በጸናጽል በእግዚአብሔር
ፊት በሙሉ ኃይላቸው ይጫወቱ ነበር።
መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ
10፥12 ንጉሡም ከሰንደሉ እንጨት ለእግዚአብሔር ቤትና
ለንጉሡ ቤት መከታ፥ ለመዘምራኑም መሰንቆና በገና
አደረገ እስከ ዛሬም ድረስ እንደዚያ ያለ የሰንደል እንጨት
ከቶ አልመጣም አልታየምም።
መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ
3፥15 አሁንም ባለ በገና አምጡልኝ አለ። ባለ በገናውም
በደረደረ ጊዜ የእግዚአብሔር እጅ መጣችበት
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ
13፥8 ዳዊትና እስራኤል ሁሉ በቅኔና በበገና በመሰንቆና
በከበሮ በጸናጽልና በመለከት በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ
ኃይላቸው ይጫወቱ ነበር።
15፥16 ዳዊትም በዜማ ዕቃ በመሰንቆና በበገና
በጸናጽልም እንዲያዜሙ፥ ድምፃቸውንም በደስታ ከፍ
እንዲያደርጉ መዘምራኑን ወንድሞቻቸውን ይሾሙ ዘንድ
ለሌዋውያን ኣለቆች ተናገረ።
15፥21 መቲትያ፥ ኤልፍሌሁ፥ ሚቅኒያ፥ ዖቤድኤዶም፥
ይዒኤል፥ ዓዛዝያ ስምንት አውታር ባለው በገና ይዘምሩ
ነበር።
15፥28 እንዲሁ እስራኤል ሁሉ ሆ እያሉ ቀንደ መለከትና
እምቢልታ እየነፉ፥ ጸናጽልና መሰንቆም በገናም እየመቱ፥
የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት አመጡ።
16፥5 አለቃው አሳፍ ነበረ ከእርሱም በኋላ ዘካርያስ፥
ይዒኤል፥ ሰሚራሞት፥ ይሒኤል፥ መቲትያ፥ ኤልያብ፥
በናያስ፥ ዖቤድኤዶም፥ ይዒኤል በመሰንቆና በበገና
አሳፍም በጸናጽል ይዘምሩ ነበር።
25፥1 ዳዊትና የሠራዊቱ አለቆችም ከአሳፍና ከኤማን
ከኤዶታም ልጆች በመሰንቆና በበገና በጸናጽልም ትንቢት
የሚናገሩትን ሰዎች ለማገልገል ለዩ በአገልግሎታቸውም
ሥራ የሠሩ ሰዎች ቍጥር ይህ ነበረ።
25፥6 እነዚህ ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት በጸናጽልና በበገና
በመሰንቆም ይዘምሩ ዘንድ፥ በእግዚአብሔርም ቤት
ያገለግሉ ዘንድ ከአባታቸው እጅ በታች ነበሩ አሳፍም
ኤዶታምም ኤማንም ከንጉሡ ትእዛዝ በታች ነበሩ።
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ
5፥12 መዘምራንም የነበሩት ሌዋውያን ሁሉ፥ አሳፍና
ኤማን ኤዶታምም ልጆቻቸውም ወንድሞቻቸውም፥ ጥሩ
በፍታ ለብሰው ጸናጽልና በገና መሰንቆም እየመቱ
በመሠዊያው አጠገብ በመሥራቅ በኩል ቆመው ነበር
ከእነርሱም ጋር መቶ ሀያ ካህናት መለከት ይነፉ ነበር።
ካህናቱም ከመቅደሱ በወጡ ጊዜ፥
9፥11 ንጉሡም ከሰንደሉ እንጨት ለእግዚአብሔር ቤትና
ለንጉሡ ቤት ደርብ፥ ለመዘምራኑም መሰንቆና በገና
አደረገ እንደዚህም ያለ በይሁዳ ምድር ከቶ አልታየም
ነበር።
20፥28 በበገናም በመሰንቆም በመለከትም ወደ
ኢየሩሳሌም ወደ እግዚአብሔርም ቤት ገቡ።
29፥25 ይህንም ትእዛዝ እግዚአብሔር በነቢያቱ እጅ
አዝዞአልና እንደ ዳዊትና እንደ ንጉሡ ባለ ራእይ እንደ
ጋድ፥ እንደ ነቢዩም እንደ ናታን ትእዛዝ፥ ጸናጽልና በገና
መሰንቆም አስይዞ ሌዋውያንን በእግዚአብሔር ቤት
አቆመ።
መጽሐፈ ነህምያ
12፥27 የኢየሩሳሌምንም ቅጥር በቀደሱ ጊዜ ቅዳሴውን
በደስታና በምስጋና በመዝሙርም በጸናጽልም በበገናም
በመሰንቆም ለማድረግ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጡአቸው
ዘንድ ሌዋውያኑን በየስፍራቸው ሁሉ ፈለጉ።
መዝሙረ ዳዊት
33፥2 እግዚአብሔርን በመሰንቆ አመስግኑት፥ አሥር
አውታርም ባለው በበገና ዘምሩለት።
43፥4 ወደ እግዚአብሔር መሠዊያ፥ ጕልማስነቴንም ደስ
ወዳሰኛት ወደ አምላኬ እገባለሁ አቤቱ አምላኬ፥ በበገና
አመሰግንሃለሁ።
49፥4 ጆሮዬን ወደ ምሳሌ አዘነብላለሁ፥ በበገናም
ምሥጢሬን እገልጣለሁ።
54፥0 ለመዘምራን አለቃ በበገናዎች ዜፋውያን መጥተው
ለሳኦል፦ እነሆ ዳዊት በእኛ ዘንድ ተሸሽጓል ብለው
በነገሩት ጊዜ የዳዊት ትምህርት።
55፥0 ለመዘምራን አለቃ በበገናዎች የዳዊት ትምህርት።
57፥8 ክብሬ ይነሣ፥ በገናና መሰንቆም ይነሡ እኔም
ማልጄ እነሣለሁ።
61፥0 ለመዘምራን አለቃ በዎች የዳዊት መዝሙር።
67፥0 ለመዘምራን አለቃ በበገናዎች የዳዊት መዝሙር።
71፥22 እኔም በበገና ስለ እውነትህ አመሰግንሃለሁ
የእስራኤል ቅዱስ አምላክ ሆይ፥ በመሰንቆ
እዘምርልሃለሁ።
76፥0 ለመዘምራን አለቃ በበገናዎች ስለ አሦራውያን
የአሳፍ የምስጋና መዝሙር።
81፥2 ዝማሬውን አንሡ ከበሮንም ስጡ፥ ደስ
የሚያሰኘውን በገና ከመሰንቆ ጋር
92፥3 አሥር አውታር ባለው በበገና፥ ከምስጋና ጋርም
በመሰንቆ።
108፥2 በገና ሆይ፥ ተነሥ፥ መሰንቆም እኔም ማልጄ
እነሣለሁ።
144፥9አቤቱ፥ አዲስ ቅኔ እቀኛልሃለሁ አሥር አውታር
ባለው በገና እዘምርልሃለሁ።
150፥3 በመለከት ድምፅ አመስግኑት በበገናና በመሰንቆ
አመስግኑት።
የዮሐንስ ራእይ
5፥8 መጽሐፉንም በወሰደ ጊዜ አራቱ እንስሶችና ሀያ አራቱ
ሽማግሌዎች በበጉ ፊት ወደቁ፥ እያንዳንዳቸውም በገናንና
የቅዱሳን ጸሎት የሆነ ዕጣን የሞላበትን የወርቅ ዕቃ ያዙ።
14፥2 እንደ ብዙ ውኃም ድምፅና እንደ ታላቅ ነጐድጓድ
ድምፅ ያለ ከሰማይ ድምፅን ሰማሁ፥ ደርዳሪዎችም በገና
እንደሚደረድሩ ያለ ድምፅ ሰማሁ።
15፥2 በእሳትም የተቀላቀለውን የብርጭቆ ባሕር
የሚመስለውን አየሁ፥ በአውሬውና በምስሉም በስሙም
ቍጥር ላይ ድል ነሥተው የነበሩት የእግዚአብሔርን በገና
ይዘው በብርጭቆ ባሕር ላይ ሲቆሙ አየሁ።
18፥22 በገና የሚመቱና የሚዘምሩም ድምፅ እንቢልታንና
መለከትንም የሚነፉ ድምፅ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ
ውስጥ ከቶ አይሰማም፥ የእጅ ጥበብም ሁሉ አንድ
ብልሃተኛ እንኳ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ
አይገኝም፥ የወፍጮ ድምጽም ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ
ውስጥ ከቶ አይሰማም፥
ትንቢት ለመናገር
ቅዱስ ዳዊት የተናገራቸው ቃለ ትንቢቶች በሙሉ
መመልከት ወይም ማንበብ በቂ ነው፡፡
“ወደዚያ ወደ ከተማይቱ በደረስህ ጊዜ፥ በገናና ከበሮ
እምቢልታና መሰንቆ ይዘው ትንቢት እየተናገሩ ከኮረብታው
መስገጃ የሚወርዱ የነቢያት ጉባኤ ያገኙሃል” 1ኛ መ.
መሳ. 10፡5 እንዲል፡፡
ከመናፍስት ሥቃይ ለመዳን
” እንዲህም ሆነ ከእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ መንፈስ
በሳኦል
ላይ በሆነ ጊዜ ዳዊት በገና ይዞ በእጁ ይመታ ነበር፡፡ ክፉ
መንፈስም ከእርሱ ይርቅ ነበር” (1ኛሳሙ.16፡23)
እንዲል፡፡
የሀገር ሉዓላዊነት ለመግለጽ … ወዘተ ይጠቅማል፡፡
“ፈረሱ አባ ታጠቅ ስሙ ቴዎድሮስ….. እኔ መዩ ቱርክን
ባይ የምሸሽ ነኝ ወይ….” እንደ ምሳሌ ልንወስደው
እንችላለን፡፡
የበገና አቀራረብ ዘዴዎች፡-
በገና በሁለት መልኩ ሊቀርብ ወይ ሊደረደር ይችላል፡፡
1. በእጅና፡-
2. በድሕንጻ፡- (ድሕንጻ፡- መግረፊያ ሆኖ እጅግ መሳጭና የበለጠ በሚመስጥ መልኩ በገናውን የሚያስጮኽ nጥንታዊ የዜማ መሣርያ ወይም የበገና ማጫወቻ ነው)
“በድሕንጻ መንፈስ ዝብጢ አውታረ መሰንቆሁ ለልብየ
ወአስተንፍሲ ውስተ አፉየ ከመ እኩን እንዚራሁ
ለበኩርኪ……) እንዲል (መጽሐፈ ሰዓታት፡ እሴብሕጸጋኪ ይመልከቱ)
ከበገና ምሳሌያዊ ትምህርቶች፡-
ላይኛው፡- የፈቃደ እግዚአብሔር
ታችኛው፡- የማኅፀነ ድንግል
ግራና ቀኙ፡- የሚካኤልና የገብርኤል
አሥሩ አውታር፡- የዓሠርቱ ቃላት
አውታሩ በእጅ ሲመታ ሁለቱም ማለትም አውታሩንና እጁን ተዋሕደው ድምፁ የሚሰማው ከታችኛው (ከቆዳው) ዘንድ እንደ ሆነ ሁሉ መለኮትና ሥጋ ተዋሕደው ከማኅፀነ ድንግል ዘንድ ለማደራቸው ምሳሌ ነው፡፡
አንድም፡-
ላይኛውና ታችኛው፡- የሰማይና የምድር ግራና ቀኙ፡- የብሉይና የሐዲስ
አሥሩ አውታር፡- የዓሠርቱ ትእዛዛት
በብሉይ ኪዳን ፈጣሪና ፍጡርን የሚያገናኙ ዓሠርቱ ትእዛዛት ስለነበሩ በዚሁ ተመስሏል፡፡
የዚህ ታሪካዊና
ጥንታዊ የዜማ መሣርያ ጣዕም ለሥርዓተ አምልኮ፣
ለልመናና ለምስጋና ተጠቅመንበት ሕይወታችን በንስሐ
መርተን ፍጻሜአችን ያማረ የተስተካከለ እንዲሆንልን
አምላከ ዳዊት እግዚአብሔር ይርዳን፤ የወላዲተ አምላክ
ድንግል ማርያም ጣዕም በአንደበታችን ፍቅርዋንም
በልቡናችን ይሣልልን፡፡ አሜን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር
ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቀጥተኛዋ መንገድ ናት
የመረጃ ምንጭ፡-ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቀጥተኛዋ መንገድ ናት ፔጅ እና ዊክፒድያ
234
People Reached
20
Engagements
Boost Unavailable
3
1 Share
Like

Comment
Share

Comments

Press Enter to post.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *