[ ]
✍በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ (በድጋሚ ፓስት የተደረገ)
♥ ቅዱስ ሚናስ በመላው ዓለም በተለይ በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ልክ እንደ ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ በእጅጉ የሚወደድ ተአምር አድራጊው (wonder-worker) በመባል የሚታወቅ ሰማዕት ሲኾን በተማፀኑት ጊዜ በምልጃው ፈጥኖ ይደርሳል፡፡
♥ ይኸውም ከደጋግ ቤተሰቦች የተገኘ ሲኾን እናቱ ልጅ ስላልወለደች በእመቤታችን በዓል ዕለት ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብታ በዕንባ መልካም ልጅን ይሰጣት ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እንድትለምንላት ተማፀነቻት፤ ያን ጊዜ ከእመቤታችን ሥዕል አሜን የሚል ቃል ተሰማ፡፡ ከዚያም ይኽነን ለባሏ ነገረችው፤ ከዚያም እግዚአብሔር የተባረከውን ልጅ በ285 ዓ.ም ላይ ሰጣት፤ ስሙንም ከእመቤታችን ሥዕል “አሜን” የሚል ቃል ስለተሰማ ርሱንም ሚናስ ብለው ሠይመውታል፡፡
♥ ዜና ገድሉ Mina was his original name, according to the story his mother called him “Mēna” because she heard voice saying amēn. Minas [Μηνας] is how he is known in Greek, while in Armenian and Arabic he is known as “Mīna” [مينا].
ይላል፤ እነርሱም የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በስፋት አስተማሩት፤ በዐሥራ ኹለት ዓመቱ አባቱ ሲያርፍ ከሦስት ዓመት በኋላ እናቱ ዐርፋ ቅዱስ ሚናስ ብቻውን ቀርቷል፤ ከዚያም መኳንንቱም አባቱን ይወድዱት ስለነበር በአባቱ ፈንታ ምስፍናን ሾሙት፡፡
♥ ዲዮቅልጥያኖስ ክርስቶስን በካደ ጊዜ ቅዱስ ሚናስ ሹመቱን ትቶ ወደ ገዳም ገብቶ ተጋድሎን ጀመረ፤ ከዕለታት ባንዳቸው ሰማይ ተከፍቶ ሰማዕታትን የብርሃን አክሊልን ሲቀዳጁ ተመለከተ ከዚኽ በኋላ ወደ ከተማ ተመልሶ ስለ ክርስቶስ አምላክነት መሰከረ፤ መኰንኑ ቅዱስ ሚናስ በወገን የከበረ መኾኑን ያውቃልና ብዙ የሹመት ቃል ኪዳን ቢገባለትም ከክርስቶስ ፍቅር ሊለይ እንደማይችል ነገረው፤ ያን ጊዜ ብዙዎች ሥቃያት አድርሶበት ስለሰለቸው ራሱን በሰይፍ እንዲቈርጡት አዝዞ ኅዳር ዐሥራ ዐምስት የሰማዕትነትን አክሊል ተቀዳጀ።
♥ የሰማዕትነት አክሊል ሲቀዳጅ ከሰማይ “ሚናስ ንኡድ ክቡር ነኽ፤ ከልጅነትኽ ዠምሮ የቅድስናን ሕይወት በመምረጥ ሦስት አክሊላትን ሰጥቼኻለኊ፤ አንደኛው ስለቅድስናኽ፣ ኹለተኛው ስለ ብቸኝነትን፤ ሦስተኛው ስለ ሰማዕትነትኽ” የሚል ድምፅን ከጌታችን ሰምቷል፡፡
♥ ከዚያም መኰንኑ የቅዱስ ሚናስ ሥጋ ወደ እሳት እንዲጣል ቢያስደርግም እሳት ፈጽሞ ሥጋውን ሊነካ አልቻለም፤ ምእመናንም ሥጋውን ወስደው ባማሩ ልብሶች ገንዘው አኖሩት፤ የመርዩጥ አገር ሰዎች ሰራዊትን ሊአከማቹ ስለወደዱ ምልጃው ይረዳቸው ዘንድ የቅዱስ ሚናስን ሰውነት ወሰዱ፤ እነርሱም በባሕር በመርከብ ውስጥ ሳሉ ፊታቸው እንደ ከይሲ አንገታቸው እንደ ግመል አንገት ያሉ አውሬዎች ከባሕር ወጥተው አንገታቸውን ወደ ሚናስ ሥጋ በዘረጉ ጊዜ ከሰውነቱ እሳት ወጥታ እነዚያን አራዊት አቃጥላቸዋለች፤ ሰዎቹም ይኽነን አይተው በእጅጉ ተደንቀዋል፡፡
♥ ወደ እስክንድርያ ደርሰው ሥራቸውን ፈጽመው ወደ ሀገራቸው በሚመለሱ ጊዜ የቅዱስ ሚናስን ሥጋ ከርሳቸው ጋር ሊወስዱ ወድደው በገመል ላይ በጫኑት ጊዜ ገመሉ ከቦታው የማይነሣ ኾነ፤ ኹለተኛም ሌላ ገመል ቢጭኑ ርሱም የማይነሣ ኾነ፤ ስለዚኽ ዛሬ ድረስ የቅዱስ ሚናስ ሥዕል ሲሳል እነዚኽ ገመሎች አብረው ይሳላሉ፤ እነርሱም ያ ቦታ እግዚአብሔር የፈቀደለት ቦታ መኾኑን ዐውቀው የከበረ ሥጋውን በዚያው አኖሩት፤ ከዚያም ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ታንጾለት ሰኔ ዐሥራ ስምንት ቅዳሴ ቤተ ክርስቲያኑ ተፈጽሞ ብዙዎች ድንቆች ተደርገዋል። ቅዱስ ሚናስ የተጓዦችና የነጋድያን ጠባቂ፧ የሕሙማን ፈዋሽ በመባል ይታወቃል።
♥ ብዙዎች ሕሙማን የከበረ ሥጋውን እየዳሰሱ ሲፈወሱ በቦታው ሳለኊ በዐይኖቼ ተመልክቼያለኊ፤ ዛሬም የከበረ ዐፅሙ በግብጽ ይገኛል፤ እኔም ለሐዋርያዊ አገልግሎት ግብጽ በኼድኩበት ጊዜ በእግዚአብሔር ፈቃድ የቅዱስ ሚናስን የከበረ ሥጋ ለመንካትና ለመጸለይና ሻማ ለማብራት ችያለኊ፡፡
♥ የኢትዮጵያ ቀደምት ሊቃውንት ቅዱስ ሚናስን አመስግነው አይጠግቡም ነበር፤- በተለይ ቅዱስ ያሬድ በድጓው ላይ በእጅጉ ያወደሰው ሲኾን ለምሳሌ ያኽል፡-
✍“ብፁዕ አንተ ሚናስ ዘመነንከ ክብረ ዘበምድር ወኀረይከ ዘበሰማይ ወኮንከ ሐራሁ ለክርስቶስ”
(የምድር የኾነ ክብርን ንቀኽ የሰማይ ክብርን የመረጥኽ የክርስቶስ ጭፍራው የኾንኽ ሚናስ አንተ ንኡድ ክቡር ነኽ)፡፡
✍“ሚናስ ኅሩይ በታዕካ ሰማይ ገጹኒ ብሩህ ከመ ፀሓይ በብዙኅ ሰላም አዕበዮ እግዚአብሔር”
(በሰማይ አዳራሽ የተመረጠው ሚናስ፤ ፊቱም እንደ ፀሓይ ብሩህ ነው፤ ብዙ በኾነ ሰላም እግዚአብሔር ከፍ ከፍ አደረገው) ይለዋል (ድጓ ዘሚናስ)
♥ ሊቁ ዐርከ ሥሉስም ይኽነን የቅዱስ ሚናስን ተጋድሎውን፦
✍“ሰላም ለከ ሐራዊ መስፍን
ሰማዕተ መድኅን
ዘሰመየተከ ሚናስ ዘጾረተከ ማሕፀን
አመ ጸለየት ጸሎተ እንዘ ይእቲ መካን
እምሥዕለ ማርያም ሰሚዐ ዘይቤ አሜን”
(መካን ሳለች ጸሎትን እየጸለየች ሳለች ከእመቤታችን ማርያም ሥዕል አሜን የሚልን ቃልን ሰምታ የተሸከመችኽ ማሕፀን ሚናስ ብላ የሰየመችኽ የመድኅን ክርስቶስ ምስክር፤ የጦር መኰንን ለኾንኽ ላንተ ሰላምታ ይገባል) በማለት ቅዱስ ሚናስን አወድሶታል፡፡
♥ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም በመጽሐፉ ላይ፡-
“ሰላም ለሚናስ ኅሩይ ዘክርስቶስ ሐራይ
ጽድቀ ዘአብደረ እምነ ንዋይ፤
አምሳለ ወርኅ ወከመ ፀሓይ ብሩህ”፡፡
(የክርስቶስ ምርጥ ጭፍራ ከገንዘብ ይልቅ ጽድቅን የመረጠ እንደ ምሳሌው እንደጨረቃ ለደመቀና እንደ ፀሓይም ብሩህ ለኾነ ለሚናስ ሰላምታ ይገባል) በማለት አወድሶታል፡፡
♥ በግብጽ ያለውን የቅዱስ ሚናስ የከበረ ሰውነቱን ስዳስስ እጅግ ልዩ የበረከት የደስታ ስሜት ውስጤን ጎብኝቶታል፤ ልዑል እግዚአብሔር ቢፈቅድ ቦታው ድረስ ኼዳችኊ ያን ልዩ በረከት እንድትሳተፉ እመኛለኊ፡፡
የቅዱስ ሚናስ በረከት ይደርብን፡፡
ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ

ቴሌግራም ቻናል፦ https://t.me/joinchat/AAAAAFTyR7tztt08pN9U-w

💥 እናንተም በረከቱ እንዲያድርባችሁ በአስተያየት መስጫው ላይ ለቅዱስ ሚናስ ምስጋናን አቅርቡለት።
Image may contain: 1 person