††† እንኳን ለዓለም ሁሉ መምሕር ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እና ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††
††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††
††† ለቤተ ክርስቲያን የብርሃን ምሰሶ ስለሆነላት ስለ ታላቁ ሐዋርያዊ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ምን እላለሁ? ምንስ እናገራለሁ? እንደ እኔ ያለ ኃጥእ: ለባሴ ሥጋና ገባሬ ንስሃ ስለሱ ሊናገር አይቻለውምና:: አባቶቻችን እንደ ነገሩን ስለ አፈ ወርቅ ለመናገር አፈ ወርቅ መሆን ያስፈልጋል:: እስኪ በቅዱሱ አባት ምልጃ ጥቂት ልሞክር::
††† ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ማን ነው?
††† ነገዱ ከሶርያ: የተወለደው በ347 ዓ/ም በእስክንድርያ ሲሆን አባቱ አስፋኒዶስ እናቱ ደግሞ አትናስያ ይባላሉ:: እነርሱ ደግ ቢሆኑ ይህንን እንቁ ልጅ እግዚአብሔር ሰጣቸው:: ዮሐንስ ለክርስቲያን እንደሚገባ በትምሕርትና በጥበብ አደገ:: ገና በሕጻንነቱ ወደ ግሪክ ሔዶ የዘመኑን ሳይንስ (ፍልስፍና) ከአፉ እስከ ገደፉ ተምሮ ተመልሷል::
ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅን ለየት ከሚያደርጉት ነገሮችም አንዱ ይሔው ነው:: በዘመናዊም ሆነ በመንፈሳዊ ትምሕርት ይህ ቀረህ የማይሉት ሊቅ የሆነው ገና በ15 ዓመቱ ነበር:: በ2 ወገን የተሳለ ሰይፍ በመሆኑ ስንኩዋን በሕይወተ ሥጋ እያለ ዛሬም ለንፉቃን ትልቅ የራስ ምታት ነው::
ቅዱሱ ገና በ16 ዓመቱ ሃብት: ንብረት: ውበት: ክብርና እውቀት የሞላለት ቢሆንም ያለውን ሁሉ ለነዳያን ሰጥቶ መጻሕፍትን ብቻ ሰብስቦ ከባልንጀራው ቅዱስ ባስልዮስ ጋር በርሃ ገባ:: ሰውነቱን በጾምና በጸሎት እየቀጣ በበርሃ ሲኖር ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስና ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ዼጥሮስ ወደ እርሱ መጡ:: ሊቀ ሐዋርያት የመንግስተ ሰማያትን መክፈቻ ስልጣን ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌሉን ሰጥተው ተሰወሩት::
ከዚህች እለት በሁዋላ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ባሕረ ምስጢራት ሆነ:: ብሉይ ከሐዲስ: ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ራዕየ ዮሐንስ ድረስ በአንድምታ ትርጉዋሜ ተነተናቸው:: በተለይ ሐዲስ ኪዳንን እየመላለሰ አመሰጠረው:: ቅዱስ ሕሊናው ሳይታክት: ንጹሕ እጆቹ ሳይዝሉ የጻፋቸው ድርሳናት: መልዕክታትና ትርጉዋሜያት ቢቆጠሩ አሥር ሺህ ሞሉ:: በእውነት ለዚህ አንክሮ ይገባል! የሚገርመው ይህን ሁሉ ሲሰራ እድሜው ገና ለጋ: ማዕርጉም ዲቁና ነበር::
ከዚህ በሁዋላ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ቅስና ተሹሞ በስብከተ ወንጌል ብዙ ቦታዎችን አዳረሰ:: በቅድስናው ወደውታልና የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ አድርገው ሾሙት:: አፈ ወርቅ ሲናገርም ሆነ ሲያስተምር እንኩዋን የሚያወራ ኮሽ የሚል የለም:: ከጣዕመ ትምሕርቱ የተነሳ ሕዝቡ በተደሞ ይሰሙት ነበር:: ሲያስተምር ምድራዊው ሰው ይቅርና ልዑላኑ መላእክት ተሰብስበው ያደንቁት ነበር:: አንዴም እመቤታችን በሕዝብ መካከል አፈ ወርቅ ብላ ጠርታዋለች:: ለዛም ነው አፈ ወርቅ የሚባለው:: ቅዱሱ በሥልጣነ ቃሉ መልዐከ ሞትን ገስፆ 10 ዓመት አቁሞታል::
ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ለሰው ፊት አያደላም:: በርሱ ዘንድ ንጉሥና ደሃ ነዳይ እኩል ነው:: ለሞት ያበቃውም ይሔው ነበር:: ምክንያቱም የወቅቱ ንግስት አውዶክስያ ያንዲት ድሃ መበለትን መሬት ቀምታ አልመልስም በማለቷ መክሮ አወገዛት:: እርሷ ግን ከኃጥአንና መናፍቃን ጋር መክራ 2 ጊዜ አጋዘችው:: በተሰደደበት ሃገር ፍሬ አፍርቶ: አስተምሮና አሳምኖ በ407 ዓ/ም አርፏል:: ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ሳይጠግቡት እንደናፈቁት በ60 ዓመቱ አጡት:: በወቅቱ ታላቅ ሐዘንና ለቅሶ ተደረገ::
አንድ ቀን የዘመኑ ደግ ንጉሥ አርቃድዮስ ግብር አገባ:: (ግብዣ አዘጋጀ) በዚያች ሌሊት ደግሞ ቅዱሱ ሊቅ ታጥቆ ሲጸልይ ሳለ: አባ ማርዳሪ የሚባል ጻድቅ ደግሞ 12ቱ ሊቃነ መላእክት (እነ ቅዱስ ሚካኤል) ከሰማይ በግርማ ሲወርዱ ተመለከተ::
ደንግጦ “ወዴት ናችሁ ጌቶቼ” ቢላቸው “ቁስጥንጥንያ: ወደ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እንሔዳለን:: እርሱ እመቤታችንን እንደሚያመሰግናት ጌታ ነግሮናልና” አሉት:: “እባካችሁ እኔም የአፈ ወርቅ ምስጋናው እንዲገለጥልኝ መርቁኝ” አላቸው:: ሊቃነ መላእክቱም መርቀውት ጐዳናቸውን ቀጠሉ::
በማግስቱ በቤተ መንግስት ውስጥ ሊቃውንቱ: መሳፍንቱ: ዻዻሳቱ: ሕዝቡ ሁሉ ተሰብስበው ከድግሱ በሉ:: ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ግን በመንበሩ ተቀምጦ ነበር እንጂ አልበላም:: ድግሱ ሲጠናቀቅ ንጉሡ አርቃድዮስ ሊቁን “ጥያቄ አለኝ” ብሎ በጉባኤ መካከል ጠየቀው::
“ምነው ወንጌላዊ ማቴዎስ ‘ኢያዕመራ ዮሴፍ እስከ አመ ወለደት ወለደ ዘበኩራ – የበኩር ልጇን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም’ ማለቱ (ማቴ. 1:25) ስለ ምን ነው?” ቢለው ቅዱሱ ተነስቶ: በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ይተረጉምለት ጀመር::
“ድንግል ማርያም ንጹሕ ብርሌን ትመስላለች:: ብርሌ የተለያየ ቀለም ያለው ፈሳሽ ቢያስገቡበት ቀለሙ አብሮ ይቀያየራል:: እመቤታችንም ጌታን ጸንሳለችና ሕብረ መለኮቱ ሲለዋወጥ መልኩዋ አብሮ ሲለዋወጥ እያየ ዮሴፍ ይደነግጥ ነበር::
‘እርሷ ማን ናት? በማሕጸኗ ያለውስ ማን ነው?’ እያለ ይጨነቅ ነበር:: ጌታን ከወለደች በሁዋላ ግን አንድ ሕብረ መልክ ሆናለችና:: አስቀድሞ ማን እንደ ነበረች አላወቀም::
አሁን ግን እርሷም ወላዲተ አምላክ: ልጇም አምላክ ዘበአማን መሆኗን አወቀ ማለት ነው” እያለ ሲተረጉም ሰምተው ሁሉም ሲያደንቁ: በዚያ የነበረች ስዕለ አድኅኖ “አፈ ወርቅ! ልሳነ ወርቅ! አፈ በረከት!” ስትል ተናገረች::
ያን ጊዜ አርቃድዮስ የወርቅ ልሳን በሊቁና በስዕሏ ላይ አደረገ:: አፈ ወርቅ ግን ባጭር ታጥቆ “እሰግድ ለኪ! እሰግድ ለኪ! ወእዌድሰኪ . . .” ብሎ ዛሬ በተአምረ ማርያም የምናውቀውን ምስጋና ሰተት አድርጐ አደረሰላት:: ይህንን ምስጋናም ሊቃነ መላእክቱ ሰምተው እያደነቁ ወደ ሰማይ ወጥተዋል::
ሊቁ ባረፈ በ35 ዓመቱ በትንሹ ቴዎዶስዮስ ዘመን: በዚህ ቀን ሥጋው ፈልሷል:: ወደ ቁስጥንጥንያ ሲደርስም ከናፍቆት የተነሳ ታላቅ ዝማሬና እንባ ተደርጉዋል:: አፈ ወርቅም ቀና ብሎ ሕዝቡን ባርኩዋል::
††† ቅዱሱ ሲጠራ እንዲሕ ነው:-
*ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
*አፈ በረከት
*አፈ መዐር (ማር)
*አፈ ሶከር (ስኩዋር)
*አፈ አፈው (ሽቱ)
*ልሳነ ወርቅ
*የዓለም ሁሉ መምሕር
*ርዕሰ ሊቃውንት
*ዓምደ ብርሃን (የብርሃን ምሰሶ)
*ሐዲስ ዳንኤል
*ሊቀ ዻዻሳት ዘበርትዕ (እውነተኛው)
*መምሕር ወመገስጽ ዘኢያደሉ ለገጽ
*ጥዑመ ቃል – – –
††† ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ ኢትዮጵያዊት †††
††† ቆራጧ እናታችን ቅድስት ወለተ ዼጥሮስ ለእኛ ለኢትዮዽያውያን የተዋሕዶ አማኞች ሞገሳችን ናት:: እጅግ የሚደነቅ መንፈሳዊ አርበኝነትን በካቶሊኮች ላይ አሳይታለችና::
ቅድስት ወለተ ዼጥሮስ የተወለደችው በ16ኛው መቶ ክ/ዘመን በምሥራቅ ኢትዮዽያ ዳውሮ አካባቢ ነው:: ወላጆቿ ባሕር አሰግድና ክርስቶስ ዕበያ ይባላሉ:: ክርስትናን በሚገባ አጥንታ አድጋ: በወላጆቿ ፈቃድ በሥርዓቱ ባል አገባች:: ግን ወዲያው አፄ ያዕቆብ ገደሉባት::
ወላጆቿም ግድ ብለው ስዕለ ክርስቶስ የተባለ የሱስንዮስን የጦር መሪ አጋቧት:: እስከ 24 ዓመቷም ልጆችን ወለደች:: በዚህ ሁሉ ጊዜ የጾምና የጸሎት ሰው ነበረች:: አፄ ሱስንዮስ ተዋሕዶን ክዶ ካቶሊክ በሆነ ጊዜ ባሏ ወደ ንጉሡ እምነት ገባ::
በዚህ ስታዝን ይባስ ብሎ ጠዳ ላይ የአቡነ ስምዓን (ዻዻሱን) ልብስ ግዳይ ይዞ ቀረበ:: እርሷም ልቧ ቆረጠ:: ፈጣሪ 3ቱን ልጆቿን አከታትሎ ወሰደ:: ደስ ብሏት ጠፍታ ሳጋ (ዛሬ ገዳሟ ያለበት) ገባች:: ቀጥላም መነኮሰች::
ከዚህ በሁዋላ እየዞረች መናፍቃን ስታሳፍር: ሕዝቡን ስታጸና ዓመታት አለፉ:: በሷ ስብከትም ብዙ መነኮሳትና ምዕመናን ሰማዕት ሆኑ:: እሷም በየገዳማቱ ተንከራተተች:: በደዌ ተሰቃየች:: በንጉሡ ተይዛ 2 ጊዜ ወደ በርሃ ተሰደደች::
ፋሲል ነግሶ: ሃይማኖት ተመልሶ ሃገር ሲረጋጋ ወደ ምጽሊ: ከዚያም ወደ መንዞ መጥታ ገዳም መሥርታ: መናንያንን ሰብስባ: ስታጽናና ኑራለች:: በተወለደች በ50 ዓመቷም በ1630ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ዐርፋ ተቀብራለች:: የተጋድሎ ዘመኗም 26 ዓመታት ናቸው:: ቅድስት ወለተ ዼጥሮስ ሰማዕትም ጻድቅም ናት::
††† የጥቡዓን አምላክ የሊቁን ምሥጢር: የቅድስቷን መጨከን: ከበረከታቸውም ይክፈለን::
††† ኅዳር 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ (ፍልሠቱ)
2.ቅድስት ወለተ ዼጥሮስ ኢትዮዽያዊት
3.አባ ሲኖዳ (ዘደብረ ጽሙና – ጐጃም)
4.ጻድቃን እለ ወጺፍ
5.ቅዱሳን አብርሃምና ሐሪክ
6.ቅድስት ወለተ ዻውሎስና ወለተ ክርስቶስ
††† ወርኀዊ በዓላት
1.እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት
2.ያዕቆብ ሐዋርያ
3.መክሲሞስና ዱማቴዎስ
4.አባ ገሪማ
5.አባ ዸላሞን
6.አባ ለትጹን
7.ቅዱስ ኤዺፋንዮስ
††† “በድካምና በጥረት: ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት: በራብና በጥም: ብዙ ጊዜም በመጦም: በብርድና በራቁትነት ነበርሁ . . . የቀረውን ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው::” †††
(2ቆሮ. 11:23)
††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††