ጥር​ ​፳፩​ ​የእመቤታችን​ ​በዓለ​ ​ዕረፍት (​አስተርእዮ​ ​ማርያም)

በቀሲስ ኃይለኢየሱስ ተመስገን

” አስተርእዮ ማርያም “

አስተርእዮ ማለት መታየት፣ መገለጥ ማለት ነው። ቃሉ አስተርአየ ታየ፣ ተገለጠ ከሚለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ነው። ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገባው ቃል ኪዳን መሠረት በሥጋ የተገለጠበት(የታየበት) ፣ አንድነት ሦስትነቱም የተገለጠበት ወቅት በመሆኑ ከልደት በዓል እስከ ጥር መጨረሻ በሙሉ ዘመነ አስተርእዮ በመባል ይታወቃል። የእመቤታችን በዓለ ዕረፍት በዘመነ አስተርእዮ ውስጥ ስለሚከበር “አስተርእዮ ማርያም” ተብሏል።

ልቡናዋ በይኩነኒ የጸና ንጽሐ ሥጋ ፣ ንጽሐ ነፍስ ፣ ንጽሐ ልቡና አስተባብራ የያዘች ወላዲተ አምላክ ምንም እንኳን የአምላክ እናት ብትሆንም ሞተ ሥጋ ለሁሉም ዕጣ ፈንታ በመሆኑ በቃል መነገሩ በልብ መታሰቡ ከፍ ከፍ ይበልና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ተንሥኢ ወንዒ”  የነፍሴ ደስታ የኾንሽ ውድ እናቴ ሆይ ተነሥተሽ ወደ እኔ ነዪ (መኃ ፪፥፲) ብሏታል።

ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኲሉ

ቅዱስ ዳዊት “ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ ሀገረ እግዚአብሔር” መዝ.፹፮፥፫ እግዚአብሔር ማህጸንሽን ከተማ አድርጎ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን የኖረብሽ ሆይ ስለ አንቺ የተነገረው የተደረገው ነገር ዕጹብ ድንቅ ነው እንዳለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአምላክ እናት ሆና ማረፏ ይደንቃል። ታላቁ የቤተክርስቲያናችን አባት ቅዱስ ያሬድ ሞቷ የሚያስደንቅ መሆኑን «ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኲሉ፤ ሞት ለማናቸውም ሰው ሁሉ የተገባ ነው የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል» በማለት ገልጾታል።

ሞት በጥር ነሐሴ መቃብር

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ሞትና ትንሣኤ በነገረ ማርያም አበው እንደሚያስረዱት ዕረፍቷ በጥር ፳፩ እሑድ ነው ። አባቶቻችን በጾመ ፍልሰታ ውዳሴ ማርያም ቅዳሴ ማርያም ሲተረጉሙ የእረፍቷን ነገር እንዲህ ብለው ይተርካሉ።

የእረፍቷስ ነገር እንደምን ነው ቢሉ ስድሳ አራት ዓመት በዚህ ዓለም ኖራ ጥር ፳፩ በእሑድ ቀን ጌታ እልፍ አዕላፋት መላእክቱን አስከትሎ መጥቶ እናቴ ሆይ ከዚህ ዓለም ድካም ላሳርፍሽ መጣሁ አላት። ልጄ ሰማይና ምድር የማይወስኑህ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማህጸኔ ተሸክሜ በድንግልና ወልጄህ እሞታለሁን? አለችው። በሲዖል የሚሰቃዩ ነፍሳትን አሳይቶ እናቴ ሆይ ሞትሽ ለእነዚህ ቤዛ ይሆንላቸዋል አላት። እሊህን ከማርክልኝስ ይሁን አለችው። ቅድስት ሥጋዋን ከቅዱስ ነፍሷ ለይቶ በቃለ አቅርንት በዝማሬ መላእክት አሳረጋት። ደቀመዛሙርቱንም ከያሉበት በደመና ጠቅሶ ካለችበት አድርሶ እመቤታችሁን ስጋዋን በክብር አሳርፉ አላቸው። ሐዋርያት በአጎበር አድርገው ወደ ጌቴሰማኒ ይዘው ሲሄዱ አይሁድ ቀድሞ ልጇን ተነሳ ዐረገ እያሉ ሲያውኩን ይኖራሉ አሁን ደግሞ እሷን ተነሳች ዐረገች እያሉ ሊያውኩን አይደለምን በእሳት እናቃጥላታለን ብለው ተነሱ። ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ ተራምዶ አጎበሩን ጨበጠው። መልአክ መጥቶ በሰይፍ ሁለት እጁን ቀጣው ከአጎበሩ ተንጠልጥሎ ቀረ። በድያለሁ ማሪኝ ብሎ ቢማጸናት እጁ ተመልሶለታል። ከዚህ በኋላ ዮሐንስን ጨምሮ በደመና ነጥቆ ከገነት አግብቶ ከዕፀ ሕይወት ሥር አኖራት።

ቅዱስ ዮሐንስን እንደምን ሆነች አሉት ከገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አለች አላቸው ቅዱስ ዮሐንስ አይቶ እኛ ሳናይ ብለው በነሐሴ መባቻ ጾም ጀመሩ ሁለት ሱባዔ ሲፈጸምም እሑድ አምጥቶ ሰጥቷቸው ቀብረዋታል በሶስተኛው ቀን ማክሰኞ “ከመ ትንሳኤ ወልዳ” እንደ ልጇ ተነሥታለች። ቅዱስ ቶማስ አልነበረም ደመና ጠቅሶ ከሀገረ ስብከቱ ሲመጣ ስታርግ አገኛት ቀድሞ የልጅሽን ትንሳኤ ሳላይ ቀረሁ ዛሬም ደግሞ ያንችን ትንሳኤ ሳላይ ቀረሁን ብሎ “ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ” ከሀዘኑ የተነሳ ሊወድቅ ወደደ እመቤታችንም አይዞህ አትዘን እሊያ ትንሳኤየን ዕርገቴን አላዩም አንተ አይተሃል ተነሣች ዐረገች ብለህ ንገራቸው ብላ የያዘችውን ሰበን ሰጥታ ሰደደችው። ከዚህ በኋላ ሂዶ የእመቤታችን ነገር እንደምን ሆነ አላቸው አግችተን ቀበርናት አሉት ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር ተው ይህ ነገር አይመስለኝም አላቸው። ቅዱስ ጴጥሮስ አንተ እንጅ ልማድህ ነው አንተ ብቻ ተጠራጥረህ አትቀርም ሰውን ሁሉ ስታጠራጥር ትኖራልህ ብሎ ተቆጥቶ ወደ መቃብሩ ሂዶ ቢከፍተው አጣት ደንግጦ ቆመ ሐዋርያው ቶማስም አታምኑኝም ብየ እንጅ እመቤታችንስ ተነሣች ዐረገች አላቸው የያዘውንም ሰበን ሰጣቸው ለበረከትም ተካፍለውታል። በዓመቱ ሐዋርያት ቅዱስ ቶማስ ትንሣኤሽን ዕርገትሽን አይቶ እኛ ሳናይ ብለው ጾም ጀመሩ በ፲፮ኛው ቀን እመቤታችንን መንበር አድርጎ ቅዱስ ጴጥሮስን ካህን ዘይትራድኦ ቅዱስ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ በዚያው ላይ ቀድሶ አቁርቧቸዋል። ቤተክርስቲያንም ይህንን መታሰቢያ አድርጋ በየዓመቱ ታከብረዋለች።

ሰአሊ ለነ ቅድስት

የኃጥአንን ለቅሶና ሐዘን አይተሽ ስለእነርሱ ድኅነት(መዳን) ዕረፍትሽን በሀሴት የተቀበልሽ እመቤታችን ሆይ ሐዋርያት በሱባዔ ትንሣዔሽን ለማየት በቅተዋልና እኛም በዓለ ዕረፍትሽን አክብረን ልጅሽ በሰጠሽ ቃል ኪዳን በቀኙ እንቆም ዘንድ ለምኝልን። አሜን።