ትህትና መንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ

++++መንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ+++++

አንድ አገልጋይ በመንፈሳዊ ሕይወቱ እየተጠቀመ መሆኑ የሚታወቀው የአገልግሎት ዘመኑ እየጨመረ ሲሄድ ትኅትናው እየጨመረ ከመጣ ነው፡፡ የአገልግሎት ብርታትና ጥንካሬ በዕውቀት መጨመር ወይም በታዋቂነት ብዛት ብቻ አይለካም፡፡ ብዙ ቦታዎችን በማዳረስና ብዙ ነገሮችንም በመሥራት ብቻ አይመዘንም፡፡ ከኢየሩሳሌም ያልወጣው ቅዱስ ያዕቆብ ነው ከሐዋርያት መካከል የመጀመሪያውን አክሊል የተቀዳጀው(የሐዋ12)፡፡ ከፊት በመምጣት ወይም ከኋላ በመነሣትም አይታወቅም፡፡ መጀመሪያ ከተጠሩት ወገን የሆነው ቅዱስ ጴጥሮስና በመጨረሻ የተጠራው ቅዱስ ጳውሎስ በአንድ ቀን ነው የሰማዕትነት አክሊል የተቀበሉት፡፡ ሊቁ አውግስጢኖስ ‹ኢየሱስ ክርስቶስ አልፋና ዖሜጋ ስለሆነ. ነው ይላል፡፡

የአገልጋይ ብቃት በዋናነት የሚለካው በትኁት ሰብእና ነው፡፡ ይበልጥ ባገለገለ ቁጥር ይበልጥ ክርስቶስን ያውቃል፡፡ ይበልጥም ክርስቶስን ባወቀ ቁጥር ይበልጥ ራሱን ያውቃል፡፡ ይበልጥ ራሱን ባወቀ ቁጥርም ይበልጥ ድካሙን ይረዳል፤ ይበልጥ ድካሙን በተረዳ ቁጥርም ይበልጥ ትኁት ይሆናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የምትጠቀመው ራሳቸውን የሚያውቁ አገልጋዮችን በማፍራት እንጂ ብዙ ነገር የሚያውቁ አገልጋዮችን በማፍራት አይደለም፡፡ ዕውቀት የሚጠቅመው ራስን በማወቅ ውስጥ ከተቀመጠ ነው፡፡ ያለበለዚያ ዕውቀት ያስታብያል(1ኛቆሮ. 8÷1)፡፡

እግዚአብሔርን አሟልቶ ማወቅ አይቻልም፡፡ ትምህርቶች ሁሉ የሚጠቅሙን እግዚአብሔርን ለማወቅ አይደለም፡፡ ስለ እግዚአብሔር ለማወቅ እንጂ፡፡ እግዚአብሔርን ማወቅ የሚቻለው ከእግዚአብሔር ጋር በመኖር ነው፡፡ ስለ እግዚአብሔር ማወቃችን የሚጠቅመን ከእግዚአብሔር ጋር መኖር እንዴት እንደሆነ ለመረዳት ነው፡፡ የተጠቀመ ሰው ስለ እግዚአብሔር ከማወቅ አልፎ እግዚአብሔርን ወደማወቅ ይሸጋገራል፡፡ አገልጋይን ስለ እግዚአብሔር ከማወቅ እግዚአብሔርን ወደማወቅ የሚያሸጋግረው ትኁት ሰብእና ነው፡፡

ይህ ትኁት ሰብእና የሚገኘውም ራስን በማወቅ ነው፡፡ ሰው ራሱን ካላወቀ እግዚአብሔርን አያውቅም፡፡ በቀኝ በኩል የተሰቀለው ሽፍታ ክርስቶስን ማወቅ የቻለው መጀመሪያ ራሱን ስላወቀ ነው፡፡ የራሱን በደልና ኃጢአት፣ የተፈረደበትም ትክክል መሆኑን ተረዳ፡፡ ስለዚህም ከጎኑ የተሰቀለውን፣ አይሁድ ወንበዴ ነው ብለው የሰቀሉትን ክርስቶስን ንጹሕ ነው ብሎ ለመመስከር፣ ‹በመንግሥትህ አስበኝ› ብሎ ለመለመን አልከበደውም፡፡ ራስህን በምእመናን ካየኸው ታላቅ ነህ፤ ራስህን በክርስቶስ ካየኸው ግን ትንሽ ነህ፡፡

ከቅዱስ ጳውሎስ ሕይወት የምንማረው ይኼንን ነው፡፡ ይበልጥ ባገለገለ ቁጥር ይበልጥ ትኁት ይሆን ነበር፡፡ ይበልጥ በተገለጠለትም ቁጥር ይበልጥ ስለ ራሱ ማንነት ይገነዘብ ነበር፡፡ የአገልግሎቱ ዘመናት በጨመሩ ቁጥር የቅዱስ ጳውሎስም ትኅትና በዚያው ልክ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ የመጀመሪያዋን መልእክቱን ለገላትያ ሰዎች በ48 ዓ.ም. አካባቢ ሲጽፍላቸው ራሱን የጠራው ‹የክርስቶስ ባሪያ› ብሎ ነው፡፡ ያ እስከ ሦስተኛው ሰማይ የተነጠቀ፣ በፍኖተ ደማስቆ በድንቅ ሁኔታ የተጠራ፣ ከእናቱ ማኅጸን የተመረጠ(ገላ.1÷15) ሐዋርያ ራሱን ‹ባሪያ› ይለዋል፡፡ በ49/50 ዓ.ም. መጀመሪያ ወደ ሮሜ ሰዎች በላከው መልእክቱ ደግሞ ‹ሐዋርያ ሊሆን የተጠራ የክርስቶስ ባሪያ› ሲል ነው ራሱን የገለጠው (ሮሜ.1÷1)፡፡ ይህ ጊዜ ብዙ ታዋቂነት ያገኘበትና የመጀመሪያ ሐዋርያዊ ጉዞውን ያደረገበት ወቅት ነው፡፡

በዚሁ ዓመት መጨረሻ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው የመጀመሪያ መልእክቱ ላይ ይበልጥ ትኅትናው ጨመረ፡፡ ራሱንም ‹ጭንጋፍ የምሆን …እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ … ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ› ሲል ገለጠው፡፡ ይህንን ያለው በልብሱ ቅዳጅ ተአምራትን ካደረገ(የሐዋ. 19÷11)፣ አጋንንት ከተገዙለትና ጉባኤው ከሰፋለት በኋላ ነው፡፡ በዓመቱ በ50 ዓ.ም. በተላከችው ሁለተኛዋ የቆሮንቶስ መልእክቱም ሰማያዊውን መገለጥ ከነገረን በኋላ ስለ ራሱ የሚሰማውን ሲነግረን ‹ማንም ከሚያይ ከእኔም ከሚሰማ የምበልጥ አድርጎ እንዳይቆጥረኝ ትቼአለሁ› ይላል (2ኛቆሮ. 12÷7)፡፡ ራሱንም እንደ ኢትዮጵያ የአብነት መምህራን ከተማሪዎቹ እንደ አንዱ አድርጎ ይቆጥራል፡፡ ከአራት ዓመታት በኋላ ለፊልጵስዩስ ሰዎች በ54 ዓ.ም. በላከው መልእክቱ እንደ ቀድሞው ራሱን ‹የክርስቶስ ባሪያ› ብሎ መጥራቱን ቀጠለ፡፡ ታዋቂው፣ ጸጋው የበዛለት፣ እስከ ሦስተኛው ሰማይ የተነጠቀው የሚለውን አልተጠቀመም፡፡ ያገኘውን ነገር የሚገልጥልን መንገር አስፈላጊ የሚሆንበት ግዳጅ ሲመጣ ነው፤ ያንንም ራስን ከመውቀስ ጋር ነው፡፡

ከዓመት በኋላ በ55 ዓ.ም. ለኤፌሶን ሰዎች በላከው መልእክቱ ላይ የቅዱስ ጳውሎስ ትኅትና ይበልጥ ጨመረ፡፡ ያፈራ ወይን፣ ያዘለዘለም ገብስ ከፍሬው ብዛት ወደ መሬት ጎንበስ ይላል፡፡ ፍሬ የሞላው አገልጋይም ትኅትናው ይጨምራል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም እንዲሁ ነው፡፡ ይህ ወቅት በሮም የታሠረበት ወቅት ነው፡፡ እርሱ ግን በፍሬው ብዛት ጎንበስ አለ፡፡ ስለ ራሱም እንዲህ አለን ‹ከዘላለም የተሠወረው የምሥጢር ሥርዓት ምን እንደሆነ ለሁሉ እገልጥ ዘንድ ይህ ጸጋ ከቅዱሳን ሁሉ ይልቅ ለማንስ ለእኔ ተሰጠ› (ኤፌ. 3÷9)፡፡ እየበቃ ሲሄድ እያነሰ መጣ፡፡ ከፍ እያለ ሲሄድ ዝቅ እያለ መጣ፡፡

በሮም እሥር ላይ እያለ ከጻፋቸው መልእክቶች አንዷ በሆነችው የ55 ዓ.ም. የፊልጵስዩስ መልእክቱ ላይ ራሱን አሁንም ‹የክርስቶስ ባሪያ› ብሎ መጥራቱን አላቆመም(ፊልጵ.1÷1)፡፡ ለብዙ ዘመናት ማገልገሉ፣ ተአምራትን ማድረጉ፣ አያሌ ምእመናንን ማፍራቱ፣ ወደ ሰማያትም መነጠቁ ከዚህ ትኅትናው አላወረደውም፡፡ ይህ ዘመን በመንፈሳዊ ሕይወቱ ትልቅ ደረጃ የደረሰበት ዘመን ቢሆን እንኳን ‹በክርስቶስ ኢየሱስ ደግሞ የተያዝኩ ያን ደግሞ እይዛለሁ ብዬ እፈጥናሉ፤ እኔ ገና እንዳልያዝኩ እቆጥራለሁ› ሲል ገና ጀማሪ ነኝ ይለናል(ፊልጵ.3÷13)፡፡ ከሦስት ዓመት በኋላ በ58 ዓ.ም. በተጻፈው የፊልሞና መልእክቱ ላይም ራሱን ‹የክርስቶስ ባሪያ› እያለ ይጠራዋል፡፡ መንፈሳዊ ዕድገትና ትኅትና አብረው ይሄዳሉና፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ በምድራዊ ሕይወቱ መጨረሻ የጻፋቸው ሁለት መልእክቶች ናቸው፡፡ በ58 ዓ.ም አካባቢ የመጀመሪያዋን፣ በ60 ዓ.ም አካባቢ ደግሞ ሁለተኛዋን መልእክት ለልጁ ለጢሞቴዎስ ልኮለታል፡፡ ይህም ለሁለት ዓመታት በሮም ከታሠረበት እሥር ቤት በወጣ ጊዜ ነው፡፡ በዚህ የሕይወቱ ዘመን ፍጻሜ ላይ ለመሥዋዕትነት እየተዘጋጀ ነው፡፡የኔሮን ጭካኔ ጨምሯል፤ በዚያ ዘመን የአውሮፓ ምዕራባዊ ጫፍ እስከሆነው ስፔን ድረስ ሄዶ በማስተማር ሩጫውን ፈጽሟል፤ የድል አክሊል ተዘጋጅቶለታል፡፡ ትኅትናው ግን ይበልጥ ጨምሯል፡፡ ስለራሱ ሲነግረንም ‹ከኃጢአተኞች ዋናው እኔ ነኝ› ይላል(1ኛጢሞ.1÷15)፡፡ ኃጢአቱ እንደተሠረየለት ያምናል፡፡ በደለኛነቱን ግን አይረሳውም፡፡ በደለኛነትን መርሳት ከትዕቢት ያደርሳልና፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለስብከተ ወንጌል ከመሠማራታቸው በፊት በአንድ ከባድ ፈተና ተፈትነው ነበር፡፡ በዚህ ፈተና ለምን እንደተፈተኑ ቅዱስ ሚካኤልን ሲጠይቁት ‹በኃጢአተኞች ላይ እንዳትፈርድባቸው ሲባል ነው› አላቸው፡፡

እውነተኛ የወንጌል አገልጋይ በመንፈሳዊ ሕይወት ማደጉን በአንድ ዋና መለኪያ ማየት ይቻላል፡፡ ይበልጥ ሲያገለግል ይበልጥ ትኁት ይሆናል፡፡

ምንጭ: አልተጠቀሰም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *