አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ-በመምህር ንዋይ ካሣሁን

ገድለ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በቪዲዮ

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ለዓለምም ሆነ ለሀገራችን ፈርጀ ብዙ በሆነ መንፈሳዊ እንዲሁም ማህበራዊ ፋይዳ ያላቸው የስልጣኔ በር ከፋች የሆኑ አባቶች የነበሯትና አሁንም ያሏት ቤተክርስቲያን ናት፡፡ ከነዚህ ታላላቅ ስራዎች ውስጥ አንዱ የሥነፅሑፍ እድገት ሲሆን ብዙ ጉልህ ድርሻ ካበረከቱት አባቶችም አንዱ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የዜማ ሊቅ ከሆነው ታላቁ ቅዱስ ያሬድ ካበረከተው የዜማ ሥርዓት ባልተናነሰ መልኩ በሥነ ጽሑፍ ረገድ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ቀዳሚ ከሆኑት ውስጥ ይጠቀሳል፡፡ በዚህም ቤተክርስቲያንን በስነ ጽሑፍ ከመጀመርያዎቹ ተርታ እንድትሰለፍ አድርጓታል፡፡

የቀደሙት ሊቃውንት በስራዎቻቸውና በጽሑፎቻቸው ልንከፍላቸው ብንሞክር የቃል ሊቃውንት እና የጽሑፍ ሊቃውንት በማለት እንከፍላቸዋለን፡፡ በዘመናቸው የክርስትና ትምህርትን ተቃውመው የተነሱትን አጽራረ ቤተክርስቲያን መጽሐፍ ጽፈው፣ በአንደበት ተናግረው የረቱ ሊቃውንትን የጽሑፍ ሊቃውንት ሲባሉ መጽሐፍቶቻቸው ትናንትናን አልፈው ዛሬም ይገስጻሉ ያስተምራሉ፡፡

የወርቃማው ዘመን አባት ኢትዮጵያዊው ጻድቅና ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የህይወት ታሪኩንና የሥነ ጽሑፍ ስራውን እጅግ ባጠረ መልኩ ለማስነበብ እንወዳለን፡፡

ልደቱ ለአባ ጊዮርጊስ

የስነ ጽሑፍ ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የተወለደው በ1357ዓ/ም በወሎ ክፍለ ሀገር በዛሬው ቦረና በጥንቱ ወለቃ ወረዳ ሸግላ ደብረ ማኃው በሚባል ቀበሌ ነበር፡፡ አባቱም ሕዝበ ጽዮን እናቱ ደግሞ እምነ ጽዮን ይባላሉ፡፡ ስለአባቱ ሁለት ዓይነት የተለያዩ ታሪኮች እናገኛለን በድርሳነ ዑራኤል መሠረት አባቱ ሕዝበ ጽዮን በመጀመርያ የትግራይ ቀጥሎም የሰግላ ወይም ጋሥጫ አገረ ገዥ እንደነበረ ያወሳል፡፡ ገድለ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ደግሞ አባቱ እግዚአብሔርን የሚወዱ የካህናት ወገን ሲሆኑ ሁለቱም እንደ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ በሕገ እግዚአብሔር የጸኑ ደጋግ ሰዎች ነበሩ፡፡ ይህ ማለት ከንጉሡ ሥዕል ቤት በቅዳሴ ወይም በማሕሌት ከሚያገለግሉ ካህናት መካከል አንዱ ነበሩ፡፡

ነገር ግን ልጅ ስላልነበራቸው ዘወትር ወደ ቤተ እግዚአብሔር በመሄድ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም እና ከሊቀ መላእክት ቅዱስ ዑራኤል ስዕል ሥር ተንበርክከው እግዚአብሔር ልጅ እንዲሰጣቸው ዘወትር ይጸልዩና ይማፀኑ ነበር፡፡ ጸሎታቸውንም ሰምቶ በመልአኩ ዑራኤል አብሣሪነት በወርኃ ሐምሌ 7ቀን ወንድ ልጅ ወለዱ ልጃቸውን ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስን በመማጸን ስለወለዱ ስሙን ጊዮርጊስ ብለው ጠሩት፡፡

አባ ጊዮርጊስ አድጎ ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ አባቱ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርቱን ካስተማሩት በኋላ መዐርገ ዲቁና እንዲቀበል ማድረጋቸውን ገድሉ ይነግረናል፡፡ ከዚህም በኋላ ለላቀ የነገረ ሃይማኖት ትምህርት የተለያዩ ሊቃውንት ወደ ሚገኙበት ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ወሰዱት፡፡ በገዳሙ ዙርያው በሐይቅ የተከበበ በመሆኑ ተማሪው አዕምሮውን ሰብስቦ ለመማር አመቺ ስፍራ ሆኖለታል፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግን በሐይቅ እስጢፋኖስ ትምህርት አልገባው ብሎት ለሰባት ዓመታት ተቀምጦ ነበር፡፡ ይህም የትምህርት ቤት ሕይወቱም ከቅዱስ ያሬድ ጋር ያመሳስለዋል፡፡ይህን የተረዱት አባ ሠረቀብርሃን እንዳይወቀሱ አባ ጊዮርጊስን ትምህርት ሊገባው አልቻለምና የቤተመንግስት ሙያ አስተምረው ብለው ወደ አባቱ መለሱት፡፡ አባቱም ልጁን የወለድኩት በስዕለት ነውና ከዚህ ገዳም እያገለገለና አባቶችን እየረዳ ይኑር ብለው ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ መልሰው አስገቡት፡፡ ከዚያም በኋላ በገዳሙ በእጅ ጥበብ ሥራ ላይ ተመደበ፡፡ የጉልበት ሥራ በመስራት ገዳሙን ያገለግልና አባቶችን ይረዳ ነበር፡፡ በጥበብ እድ ባካበተው ዕውቀትም እንደ ቅዱስ ላሊበላ ከዓለት ፈልፍሎ ቤተክርስቲያንን አንጿል፡፡ እንዲሁም የወለቃን ወንዝ ለመሻገር ያገለግል ዘንድ ከዓለት ፈልፍሎ የሠራው ድልድይም የሥነ ሕንጻ ሙያውን ያሣየበት ሥራዎቹ ናቸው፡፡

ከነዚህ የተቀደሱ ሥራዎቹ በኋላ ያለዕረፍት ሌሊቱን ሙሉ ከቅድስት ድንግል ማርያም ስዕል ሥር እልፍ አልፍ /አስር ሺህ/ግዜ በመስገድ ፈጣሪውን ይለምን ነበር፡፡ የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳምን እህል በመፍጨትም ያገለግልም ነበር፡፡ ነገር ግን አገልግሎት የሚያበረክትላቸው መነኮሳት ከማመስገን ይልቅ ትምህርት የማይገባው ድንጋይ እያሉ ይነቅፋት ጀመር፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግን እንደነቀፉኝ ልንቀፋቸው ሷይል የተለመደ ቅን አገልግሎቱን እየቀጠለ ከእመቤታችን ሥዕል ስር ተደፍቶ እመቤቴ ሆይ መነኮሳቱ በእኔ ላይ እየፈጸሙብኝ ያለውን ነቀፋና ዘለፋ ተመልክተሽ ትምህርቴን እንዲገልፅልኝ ከልጅሽ ዘንድ ለምኚልኝ እያለ ሲፀልይ አንድ ቀን እመቤታችን ተገለጠችለትና አይዞህ ዕውቀት የተሠወረብህ ትምህርት ስለማይገባህ ሳይሆን የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ እንዲገለጥ ነውና ታገስ አለችው፡፡ ከዚያም ጽዋዐ ልቡናን አጠጣችው፡፡

ከዚህ በኋላ በሐይቅ እስጢኖፋስ ትምህርቱን በሚገባ ተምሮ አጠናቀቀ በዕውቀቱም ቀድሞ የሚያውቁት ሁሉ ይደነቁበት ጀመረ፡፡ አባ ጊዮርጊስ የያሬድን ትምህርት በጥልቀት ከሚያውቁት ከጥቂት ሊቃውንት መካከል አንዱ እንደነበረ ገድሉ ያስረዳል የተማረውም ከአቡነ ሳሙኤል ዘጋማ ነው፡፡

አባ ጊዮርጊስ የቅኔም ሊቅ ነበር፡፡ ይህንንም ዕውቀቱን የምንለካው በድርሰቶቹ ሲሆን ስለዚህም ነው በቀጥታ ከቅዱስ ያሬድ ጀምሮ በሚወርደው የድጓ መምህራን ዝርዝር ውስጥ ስሙ የሚጠቀሰው፡፡ በትርጓሜ መጽሐፍት የጠለቀ ዕውቀትም እንዳለው ድርሰቶቹ ይመሰክራሉ በተለይም መጽሐፈ ምሥጢር የሚባለው መጽሐፍ የዕውቀቱን ስፋትና ጥልቀት አጉልቶ ያሳየበት ድንቅ መጽሐፉ ነው፡፡ ከላይ እንደገለጥነው የተማረበት ስፍራ ሐይቅ እስጢፋኖስ ቤተመጽሐፍቱም በብዙ መጽሐፍት የተሟላ በመሆኑ ልዩ ልዩ መጽሐፍትን በማንበብ መንፈሳዊ እውቀቱን አበልጽጓል፡፡ የሰፋ ዕውቀቱም በዘመኑ ከነበሩት ታላላቅ ሊቃውንት ስለ እምነት ተጠያቂ ከነበሩት አንዱ እንዲሆን አድርጐታል፡፡

ለምሳሌ በአጼ ዳዊት ዘመነ መንግሥት የመጣው ግብጻዊው ጳጳስ አቡነ በርተሎሜዎስ ሥላሴን አንድ ገጽ ይላሉ የሚል ጥርጣሬ ነበር፡፡ ይህንኑ ወሬ ንጉሡ አጼ ዳዊት ስለሰማ ጳጳሱን አነጋገረው ነገሩን እንዲያጣሩ ሦስት ሰዎችን ማለት ቄስ ሐፄ ተከሥተ ብርሃን፤ መምህር ዮሴፍ ከደብረ ሐይቅ፤ አበምኔትና ካህን አባ ጊዮርጊስን መርጦ ነበር፡፡ እነርሱም ጳጳሱ ዘንድ ሂደው ካነጋገሩዋቸው በኋላ ክሱ ሐሰት መሆኑን በማረጋገጥ ስለ ምስጢረ ሥላሴ የሚገልጠውን የጳጳሱን እምነቱ በጽሑፍ ይዘው መጡ አቡነ በርተሎሜዎስ ስለ ሥላሴ ያለው እምነት የጠራና የተሟላ እንደሆነ አረጋገጡ፡፡

የትምህርቱ ጥልቀትና የማስረዳት ችሎታው መልካም ስምን ያተረፈለት ስለሆነ አፄ ዳዊት ስምንት ወንድ ልጆቹን ቴዎድሮስ፣ ይስሐቅ፣ ቴዎፍሎስ፣ እንድርያስ፣ ሀብተ ኢየሱስ፤ ሕዝቅያስ፣ ኢዮስያስ፣ ዘርአ ያዕቆብ፣ እና አንዲት ሴት ልጁን እሌኒን እንዲያስተምርለት ወደ ቤተመንግስት ወሰደው፡፡ በማስተማሩም ችሎታ በተማሪዎች ዘንድ ይታወቃል፡፡ ሁሉንም በዕውቀትና በምግባር በሐይማኖት ቀርጿቸዋል፡፡ ከነርሱም ቴዎድሮስ በአንዲት ሴት ጸንቶ የኖረ በመሆኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የቅድስና ማዕረግ ተሰጥቶታል፡፡ መታሰቢያውም ሰኔ 29ቀን ይከበራል፡፡ ዘርአ ያዕቆብም በይበልጥ በስነ ጽሑፍ የመምህራን ፈለግ ተከትሏል፡፡ እርሱም እንደመምህሩ ብዙ መጽሐፍትን ደርሶ አባዝቶአቸዋል፡፡ ይስሐቅም በዘመኑ ፖለቲካዊና ባህላዊ እምርታ እሳይቷል፡፡

ምንኩስናው

አጼ ዳዊት የአባ ጊዮርጊስ ማንነት በይበልጥ የተገነዘበው በቤተ መንግስት እየኖረ ልጆቹን በሚያስተምርበት ጊዜ ነበር፡፡ የዚያን ጊዜ አባ ጊዮርጊስ አልመነኮሰም ነበርና ንጉሡ በመልካም ሥነ ምግባሩ ተማርኮ ስለነበር ሴት ልጁን አጋብቶ በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ሊያስቀምጠው ፈለገ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግን የምንኩስናን ኑሮ ስለመረጠ ጥያቄውን አልተቀበለም፡፡ ጊዮርጊስ መምህር እያለ ወደ ጳጳሱ አቡነ በርተሎሚዎስ ዘንድ ሄዶ ቅስናን ተቀበለ፡፡ ከዚያም አስከትሎ አባ በጸሎተ ሚካኤልን ከልጅነቱ ጀምሮ ይወዳቸው ስለነበር እርሳቸው በመሰረቱት ገዳም በመልካም ሥነ ምግባራቸው ከታወቁት ከአባ ቴዎድሮስ ዘንድ የምንኩስናን ልብስ ለብሶ መነኮሰ፡፡

አባ ጊዮርጊስ የሕዝብ መምህርነቱ ከዳር እስከዳር እየታወቀ ሄደ፡፡ በዚህም ብዙ ወዳጅም ጠላትም አፍርቷል፡፡ በተለይም ከቤተመንግስት ሰዎች ጋር ተጋጭቷል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ቀደም ብሎ ካህናቱ ቀድሰው ሲያቆርቡ ንግስቲቱ ስትቆርብ ካህናቱ እርሷ የተቀመጠችበት ድረስ ሄደው ያቆርቧት ነበር፡፡ ነገር ግን አባ ጊዮርጊስ ይህንን ድርጊት ተቃውሞ ከሰው ይልቅ ሊከበር የሚገባው እግዚአብሔር ነው በማለት ንግሥቲቱ ካህናቱ ድርገት የወረዱበት ድረስ መጥታ እንድትቀበል አደረጋት፡፡ ለግዜው ብትቀበለውም እያደር ግን እንደ መዋረድና መናቅ ስለቆጠረችው ነገሩን በምሬት ለንጉሡ ነግራ በድፍረቱ መቀጣት እንዳለበት አሳሰበች፡፡ አጼ ዳዊት ግን ሊያስረው ፈልጎ ነገር ግን በደንብ ያውቀው ስለነበር ንቡረ እድ ማዕረግ ሰጥቶ ወደ ዳሞት ላከው ይህንን በማድረግ ጉዳዩን በብስለት ቢፈቱትም ንግሥቲቱን አላስደሰታትም፡፡

አባ ጊዮርጊስ እና አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ የተገናኙት አባ ጊዮርጊስ ወደ ዳሞት በተጓዘበት ጊዜ ነበር፡፡ ከዚህ ግዜ በኋላ አባ ጊዮርጊስ ዋና ትኩረቱ በድርሰቱ ላይ ሆነ፡፡ በዚህ ላይ የጳጳሱን የአቡነ በርተሎሜዎስን ፈቃድ ስለፈለገ ወደ ጳጳሱ ዘንድ ሄደ፡፡ ጳጳሱም ተቃውሞ አልነበረውም፡፡ የቅዳሴ ድርሰት ማዘጋጀቱን ገድሉ ይጠቅሳል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ቅዳሴያት ደራስያኑ ማን ናቸው ብለን ምርምር እንድናደርግ ይጋብዛል፡፡ ከድርሰቱ ጋር የማስተማሩን ሥራ አጣምሮ ይሠራ ነበር፡፡ በተለይም የቤተክርስቲያንን ትምህርት በተመለከተ እርሱ ከሌለ አይሳካም፡፡ በዚያ ጊዜ በሸዋ በይፉት ራሳቸውን ቤተ እስራኤል እያሉ የሚጠሩ እይሁድ ነበሩ፡፡ ከአቡነ ዜና ማርቆስ ጀምሮ ብዙ መምህራን ወደነዚህ ሕዝቦች እየተሰማሩ ወንጌልን አስተምረዋል፡፡አቡነ ዜና ማርቆስ ወደ ክርስትና ለተመለሱት ቤተ እስራኤላውያን በእመቤታችን፣ በቅዱስ ሚካኤል፣ በአባ ኖብና፣ በሰማዕቱ በጊጋር ስም አራት አብያተ ክርስቲያናትን አሠርተው ነበር፡፡ ሁለቱ አሁንም ሲኖሩ ሌሎቹ ሁለቱ ግን የሉም፡፡

ከእነዚህ አይሁድ መካከል አንዱ ከክርስቲያኖች ጋር በነገረ ሃይማኖት ለመከራከር ጥሪ አቀረበ፡፡ “ክርስቲያኖች ከረቱኝ ወደ እነርሱ ሃይማኖት እገባለሁ እኔ ከረታኋቸው ወደ እኔ ሃይማኖት ይገባሉ”ሲል ነገሩን ጥብቅ አደረገው፡፡ አፄ ዳዊት ይህን ጉዳይ ሲሰማ በጣም ስለተናደደ ሊቃነ ካህናቱን፣ ንቡራነ እዱንና የመጻሕፍት ዐዋቂዎችን ሁሉ ከየሀገሩ እንዲሰበሰቡ አደረገ፡፡ አይሁዳዊው በአንድ ወገን መምህራኑ በአንድ ወገን ሆነው ክርክሩን አዘዘ፡፡ የመጀመርያው እድል የተሰጠው ለአይሁዳዊው በመሆኑ ቀጥሎ ያለውን ጥያቄ አቀረበ “እናንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነው የምትሉት ይህ ክርስቶስ እውነት የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነ ወደ ቢታንያ በመጣ ጊዜ አልዓዛር የተቀበረበትን ቦታ ሳያውቅ ቀርቶ አልአዛርን የት ቀበራችሁት? ብሎ እንደ ጠየቀ በወንጌላችሁ ተጽፏል፡፡ ለዚህ መልስ ሰጡኝ እኔንም ከመጽሐፈ ኦሪት ጠቅሳችሁ ጠይቁኝ” ሲል የመከራከርያ ነጥቡን አቀረበ፡፡

በዚህ ጊዜ አባ ጊዮርጊስ ታሞ አልጋ ላይ ነበር፡፡ ሊቃውንቱም እንዲህ ያለው ነገር ያለ እርሱ አይሆንምና አባ ጊዮርጊስ ይምጣ ሲሉ ለአፄ ዳዊት አመለከቱት አባ ጊዮርጊስም በአልጋ ላይ እያለ እንዲመጣ ተደረገ፡፡ ሊቁም በአልጋ ላይ ሆኖ በጉባኤው ተገኘ፡፡ ጉባዔተኞቹ የቀረበውን ጥያቄ ነገሩት፡፡ አባ ጊዮርጊስም “እኔ ግን በወንጌል ሳይሆን በኦሪት እከራከርሃለሁ የምኩራብ መጽሐፍት ሁሉ በቤተ ክርስቲያን የታወቁ ናቸውና ምኩራብ ዘራችው ቤተክርስቲያንም አጨደችው፡፡ ምኩራብ ፈተለችው ቤተክርስቲያንም ለበሰችው፡፡ አዳምን በገነት ሳለ አዳም ሆይ ወዴት ነህ ብሎ የጠየቀው ማን ነው እግዚአብሔር አብ አይደለምን”?በዚህ ጊዜ አይሁዳዊው መልስ አጥቶ ዝም አለ ንጉሡ ሊቃውንቱና መኳንንቱ እጅግ ተደሰቱ፡፡

አባ ጊዮርጊስ ሌላው ያጋጠመው ክርክር ቢቱ ከተባለው ሰው ጋር ያደረገው ክርክር ነበር፡፡ ቢቱ በምጽአት ጊዜ የሚመጣው ወልድ ብቻውን እንጂ አብና መንፈስ ቅዱስ አይመጡም በማለት ሲያስተምር የጥንቆላ ሥራንም ይሠራ ነበር፡፡ ይህንንም መናፍቅ ብዙ ታግሎታል፡፡ ነገር ግን ቢቱ ለንጉሡ በጻፈው የሀሰት ደብዳቤ አባ ጊዮርጊስን አሳስሮታል፡፡ በደም እስኪነከር ተደበደበ፡፡ ቢቱ ግን በመልአክ ተቀስፎ ሞቷል፡፡ አባ ጊዮርጊስም ለዚህ መናፍቅና ወደፊትም ለሚነሱት መሠል ከሀዲዎች መልስ የሚሆን መጽሐፈ ምሥጢር የተባለውን መጽሐፍ ጽፏል፡፡

ዕረፍቱ ለአባ ጊዮርጊስ

አፄ ይስሐቅ ሌላው የአባ ጊዮርጊስ ደቀመዝሙር ከዙፋን ላይ በወጣ ጊዜ አባ ጊዮርጊስ በደረሰበት መከራ ጤንነቱ ተዳክሞ ነበር፡፡ ይህንንው የተረዳው አፄ ይስሐቅ ምድረ ሰዎን የተባለውን ስፍራ ርስተ ጉልት፣ ሰጥቶት ነበር፡፡ ሰዎን ከጋስጫ ብዙም የራቀ ስፍራ አይደለም፡፡ ስፍራውም የጳጳሳት መቀመጫ ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ በግዞት በነበረ ጊዜ በራእዩ እመቤታችን ተገልጣ ዕረፍቱ በአባ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም እንደሚሆን እንደነገረችው ገድሉ ይተርካል፡፡ አባ ጊዮርጊስ በምድረ ሰዎን ንጉሥ ይስሐቅ ክረምቱን ያሳልፍበት በነበረው ቦታ ላይ ቤተክርስቲያን ሠራ በዚያም በማስተማርና በጾም በጸሎት ይተጋ ነበር፡፡ በጋሥጫ እያለ አፄ ይስሐቅ እስጠራው፡፡ በዚያ ጊዜ ንጉሡ የመናገሻ ማርያምን ቤተክርሰቲያን አሠርቶ ስለነበር እንዲባርክለት ፈልጎ ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ ምንም እንኳን በዚያ ጊዜ ታምሞ የተኛም ቢሆን ወደ ንጉሡ ተጓዘ፡፡ እዚያ ሲደርስ በጣም ተዳክሞ ነበር፡፡ ሥርዓቱን ለመፈጸምም ዐቅም አልነበረውም፡፡ ስለዚህ ንጉሥ ይስሐቅ በአልጋ ተሸክመውት እንዲዞሩ ቤተክርስቲያኗን እንዲባረክለት አደረገ፡፡

ቡራኬውን ከፈጸመ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን ሰብስቦ ከሞትኩ አባቴ በጸሎተ ሚካኤል መከራ ወደ ተቀበለባትና እኔም ቤተክርስቲያን ወዳነጽኩበት ቦታ ወስዳችሁ ቅበሩኝ ሲል አዘዛቸው፡፡ ለደቀ መዛሙርቱ የመጨረሻ የስንብት ትምህርት እያስተማራቸው እነርሱም በአልጋ ተሸክመውት ወደ ጋሥጫ እያመሩ ሳለ በመንገድ ላይ ሐምሌ ሰባት ቀን 1426ዓ.ም በ69 ዓመቱ ዐረፈ፡፡

አስረጅ መጽሐፍ
  • ገድለ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
  • ድርሳነ ዑራኤል
  • የቤተክርሰቲያን መዝገበ ቃላት ዶ/ር ስርግው ሀብለሥላሴ
  • መጽሐፈ ምስጢር መምህር ኃይለማርያም ላቀው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *