ዘፈን

“ዘፋኝነት” የሥጋ ሥራ ነው፡፡(ገላ.5፥21) የሥጋን ሥራ የሚያደርግ ሁሉ ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግስት አይወርስም፡፡ (1ቆሮ. 6፥11) በክርስቶስና በእግዚአብሔር መንግስትም ርስት የለውም፡፡(ኤፌ.5፥5)፡፡እርግጥ ነው በቀደመው ዘመን ሁላችን የኃጢአት ባርያዎች፤ የሞትም አገልጋዮች ነበርን፡፡ ነገር ግን ዛሬ ከዚያ ከምናፍርበትና ከምንፀፀትበት ህይወታችን ያተረፍነው ምንም ፍሬ ስለሌለን፤ መጨረሻውም ሞት እንደሆነም ስላመንን፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆነን አሁን ከኩነኔ ነፃ ነን፡፡(ሮሜ 6፥20፤8፥1) ባዕለጠጋው እግዚአብሔር ‹‹ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩም የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ህይወትን ሰጠን፤ በፀጋውም አዳነን››፡፡(ኤፌ.2፥4-6)

አዎን! በቀደመ ዘመናችን ለሁለት ጌቶች የምንገዛ ብንሆንም (ማቴ.8፥24)ዛሬ ግን ላንዱና ለሚበልጠው ጌታ በውድና በፍቅር ስለተገዛን ያ ዓለም፤አያምረንም፡፡ (ሮሜ.8፥23) ስለዚህ ያንን ዓለም በሚበልጥ ዓለም ተክተን ንቀን ጠልተነዋል፡፡ “ሰማዕታት የዚህችን ዓለም ጣዕም በእውነት የናቁት፤ ደማቸውንም ስለእግዚአብሔር መንግስት በመታገስ ያፈሰሱት” የዚህን ዓለም ጣዕም በእውነት ስላዩትን ስለናቁት ነውርም እንደሆነ ስለተረዱት ነው፡፡

ሁላችንም ከልብ የምንወደው አንድ እውነት አለ፡፡አለም “ያገነነቻቸው ብቻ ሳይሆኑ” ሁሉም ኃጢአተኞች ኃጢያታቸውን ጠልተው በንስሐ ቢመለሱ፤ እንኳን እኛ የሰማይ መላዕክትም ደስተኞች ናቸው፡፡ (ሉቃ.15፥10) አንድ ዘፋኝም ሆነ የትኛውም በተገለጠም ሆነ በድብቅ ነውርና ኃጢአት የሚመላለስ ማናቸውም ሰው “መንፈሱ በጌታ በኢየሱስ ቀን ትድን ዘንድ”(1ቆሮ.5፥5) ንስሐ ገብቶ ቢመለስ የሁላችንም መሻት ነው፡፡ በተለይ የጌታን መንግስት በቶሎና በትጋት ትመጣ ዘንድ ለምንጠባበቅና ለምንናፍቅ “ትሩፋን”፡፡

የእስራኤልን ልጆች ያረከሰው አንዱ ኃጢአት “ሊበሉ ተቀምጠው ሊዘፍኑ መነሳታቸው” ነበር፡፡ (ዘጸ.32፥6) ጌታን ያጠመቀው ቅዱሱ ነቢይ ዮሐንስ አንገቱ እንደዋዛ በሰይፍ የተመተረው ዘፈን ባመጣው ጣጣ ነው፡፡(ማቴ.14፥6) ዛሬም የብዙዎች ትዳር የሚፈርሰው፣የብዙ ሚሊየን ወጣቶች ህይወት የሚረክሰውና በአጭር የሚቀጨው ዘፋኞች በሚያቀነቅኑት “ሰይጣናዊ ዜማ” ነው፡፡የእገሌ ዘፈን “ያስታርቃልና” ተብሎ በቤተ ክርስቲያን አውድ ለመዝፈን የቃጣንና የነሸጠን ጊዜ ላለመኖሩ ምን ዋስትና አለን? እኒህ ትውልዱን ለዝሙትና ለርኩሰት የሚማግዱ ዘፋኞች ናቸው እንግዲህ “ኦርቶዶክስ እንጂ እኛ የወንጌላውያና ህብረት አማኞች አይደለንም” እያሉ “በአካኪ ዘራፍ ፉከራ” በየአደባባዩ ጉምቱ ወሬ የሚያወሩት፡፡

ጥቂት ያይደሉ ዘፋኞች ከዓመታት በፊት “መዝሙር ዘምረው” ኦርቶክሳዊ መሆናቸውን ነገሩን፡፡ከዚያ አንዳቸውንም መመለሳቸውን (በንስሐና እንደኃጢአታቸው በግልጥ ኑዛዜ) ሳንሰማ ወዲያው ዘፈን ማውጣታቸውን አብረን ሰማን፡፡ (የሎጥ ሚስት ወደኋላ ስትመለስ የጨው ሀውልት እንጂ ሥጋ መልበሷን አልሰማንም፤አላነበብንምም ነበር!!!) ዘፋኝነት የአደባባይ፤ ብዙዎችንንም የሚያሰናክል ኃጢአት ነው፡፡ የአደባባይ ኃጢአት የሠራ ተነሳሒ ኑዛዜውም በአደባባይ ሊሆን ይገባዋል፡፡ዘኬዎስና ከነናዊቷ ሴት ኃጢአታቸውን በአደባባይ ነበር የተናዘዙትና ያመኑት፡፡(ሉቃ.19፥8፤ማቴ.15፥27)

በአጭር ቃል የጌታን ቃል ደግሜ እላለሁ “ዘፋኞችና የሥጋን ሥራ የሚያደርጉ ሁሉ ደመወዛቸው ሞት እንጂ ዘላለማቸው የእግዚአብሔር መንግስት አይደለምና” የበደሉትን ህዝብ፤ በየጭፈራ ቤቱና በየመሸታ ቤቱ ያረከሱትንና ያፈረሱትን ወጣትና ትዳር በግልጥ ኑዛዜ ይቅርታ ጠይቁና ተመለሱ እንጂ ዘፋኝነትን ኦርቶዶክሳዊ ካባ አታልብሱት፡፡ እውነተኛ ኦርቶክሳዊነት ዓላማዊነትን መካድ እንጂ ከአለማዊነት ጋር በአንድ መተባበር አይደለምና … ዘፋኞች ሆይ! የግልጥ ኃጢአታችሁን፤ በሁለት ዓለምና ጌታ ማንከስን ትታችሁ መመለስ ይሁንላችሁ፡፡

አዎ! “ዘፋኝና ዘፋኝነት ለኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ላንቺም” ምንሽም አይደለምና ለቀብር እንጂ ለህይወት የማይመጡ “ልጆችሽን” ቤተ ክርስቲያን ሆይ! ተነሺና ጎብኚያቸው፤ ባዝነው የሚቅበዘበዙትንም ወደበረቱና መንጋው ሰብስቢያቸው፡፡

ጌታ በትንሳኤው ብርሐን የዘፋኝነትን መንፈስ ከምድሪቱ ያርቅልን፡፡አሜን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *