ነቢዩ ቅዱስ ኤልያስ

ነቢዩ ኤልያስ በገለአድ አውራጃ በቴስብያ፣ በእግዚአብሔር ትእዛዝና ሕግ ጸንተው ይኖሩ ከነበሩ ጻድቃን ወላጆቹ ከሌዊ ወገን ከሚኾን አባቱ ከኢያሴንዩ እና ከእናቱ ቶና ታኅሣሥ ፩ ቀን ተወለደ፡፡ በተወለደ ጊዜም እግዚአብሔር ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ መርጦታልና መላእክተ ብርሃን ሰገዱለት፤ በጨርቅ ፈንታም በእሳት ጠቀለሉት፡፡ እናትና አባቱም በኹኔታው ከመፍራታቸው የተነሣ ወደ እርሱ መቅረብን ፈሩ፡፡በስምንተኛው ቀን ሥርዓተ ግዝረት ሲፈጽሙለትም ስሙን “ኤልያስ” አሉት፡፡

ነቢዩ ኤልያስ ሕገ ኦሪትን እየተማረ ካደገ በኋላ እናቱንና አባቱን፣ ዘመዶቹንም፣ ገንዘቡንም ዅሉ ትቶ በበረሃ ተቀመጠ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ ፲፩፥፴፯-፴፰ “… ማቅ፣ ምንጣፍና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ ተጨነቁ፤ ተቸገሩ፤ መከራ ተቀበሉ፤ ተራቡ፤ ተጠሙም፡፡ ዓለም የማይገባቸው እነዚህ ናቸው፤ ዱር ለዱርና ተራራ ለተራራ፣ ዋሻ ለዋሻና ፍርኩታ ለፍርኩታም ዞሩ፤” በማለት እንደ ተገናረው ነቢዩም ከዓለማዊ ኑሮ ተለይቶ ማቅ ለብሶ በየተራራው፣ በየፍርኵታውና በየዋሻው መኖር ጀመረ /ገድለ ኤልያስ ነቢይ ዘታኅሣሥ፣ ቍ.፩-፱/፡፡

የስሙ ትርጓሜ

  • የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንደሚያስረዳው“ኤልያስ” የሚለው ስም “እግዚአብሔር አምላክ ነው” የሚል ትርጕም አለው፡፡ በመጽሐፈ ገድሉ እንደ ተጠቀሰው ደግሞ የስሙ ትርጓሜ “የወይራ ዘይት፣ የወይራ ተክል” ማለት ነው፡፡ የወይራ ዘይት በጨለማ ላሉት ዅሉ እንዲያበራ ኤልያስም ለእግዚአብሔር ቤት መብራት ነውና፡፡ እስራኤላውያን ሕገ እግዚአብሔርን በመጣስ፣ ጣዖታትን በማምለክ ጨለማ በተዋጡ ጊዜ ነቢዩ ኤልያስ ደርሶ ሰማይን በመለጎም፣ የምንጮችን ውኃ በማድረቅና ሌሎችንም ድንቅ ድንቅ ተአምራት በማሳየት ልቡናቸውን ብሩህ አድርጎ ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር መልሷቸዋልና፡፡
  • ኤልያስ ማለት“ዘይት (ቅባት)፣ መፈቃቀር” ማለት ነው፡፡ ዘይት (ቅባት) የተባለውም የሰው ፍቅር ሲኾን ይኸውም ነቢዩ ኤልያስ በገቢረ ተአምራቱ በእግዚአብሔርና በእስራኤል መካከል ሰላምንና ፍቅርን ማስፈኑን ያመላክታል /የገድለ ኤልያስ መቅድም፣ ቍ.፱-፲፱/፡፡

ነቢዩ በእግዚአብሔር ኀይል ካደረጋቸው ታላላቅ ተአምራት መካከልም ዝናም ማቆሙና ዳግመኛ እንዲዘንም ማድረጉ /፩ኛ ነገ.፲፯፥፩-፪፤ ፲፰፥፵፮-፵፰/፤ የደሃዋን ቤት በበረከት መሙላቱ /፩ኛ ነገ.፲፯፥፲፮-፳፬/፤ የሞተውን ልጅ ማስነሣቱ /፩ኛ ነገ.፲፯፥፳-፳፫/፤ በካህናተ ጣዖት ፊት መሥዋዕቱን ወደ እግዚአብሔር ማሳረጉና የጣዖቱ ካህናትን ማሳፈሩ /፩ኛ ነገ.፲፰፥፳-፵/፤ እና ጠላቶቹን በእሳት ማቃጠሉ /፪ኛ ነገ.፩፥፱-፲፫/ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

አንድ ቀን ነቢዩ ኤልያስ ጸሎት እያደረገ ሳለ መልአኩ ቅዱስ ራጉኤል ተገልጾ፡- “ኃላፊ፣ ጠፊ የኾኑ ሕሊናትን ያሸነፍህ፤ ሞትንም ድል ያደረግህ ተጋዳይ ሆይ ፈጽሞ ደስ ይበልህ፡፡ ወደ ሰማይ የምታርግበት ዘመን ደርሷልና፡፡ ፍጹም ደስታ፣ ፈገግታ፣ ተድላ ከሰፈነበት አገር ትኖራለህ፡፡ ደዌ፣ በሽታ፣ ሞት፣ ኀዘን ከሌለበት፤ በረከት፣ ከሞላበት ቤትም ትገባለህ፡፡ በዚያም የልዑል እግዚአብሔርን ትእዛዝ የሚጽፍ እንደ አንተ ያለ ሄኖክ አለ፡፡ አሁንም ተነሥና ዮርዳኖስን ተሻግረህ ሒድ” አለው፡፡

እግዚአብሔር ኤልያስን ወደ ሰማይ የሚያሳርግበት ጊዜ ሲደርስም ነቢዩ ከጌልጌላ ተነሥቶ ወደ ኢያሪኮ ሲሔድ ደቀ መዝሙሩ ኤልሳዕ “በሕያው ነፍስህ እምላለሁ፤ አንተን አልለቅህም፤” በማለት ተከትሎት ሔደ፡፡ ኢያሪኮ በደረሱ ጊዜም በኢያሪኮ ያሉ ደቂቀ ነቢያት መጡ፡፡ የኤልያስ ዕርገት በመንፈስ ቅዱስ ጥበብ ተገልጾላቸው ኤልሳዕን፡- “ዛሬ እግዚአብሔር ጌታህን ከአንተ እንደሚወስደው ታውቃለህን?›› አሉት፡፡ እርሱም፡- ‹‹አውቃለሁ፤ ዝም በሉ፤” አላቸው፡፡ ከዚያም ኤልያስ ኤልሳዕን “እግዚአብሔር ወደ ዮርዳኖስ ልኮኛልና ከዚህ ተቀመጥ” ባለው ጊዜ አሁንም “በሕያው ነፍስህ እምላለሁ፤ አንተን አልለቅህም፤” በማለት አብሮት ሔደ፡፡

ከነቢያት ወገንም አምሳ ወንዶች ከእነርሱ ጋር በአንድነት ሔደው ከፊት ለፊታቸው ቆሙ፡፡ ኤልያስም በመጠምጠሚያው የዮርዳኖስን ውኃ ቢመታው ውኀው ከሁለት ተከፈለ፡፡ ኤልያስና ኤልሳዕም ወንዙን በደረቅ ተሻገሩ፡፡ ወጥተውም ከምድረ በዳ ቆሙ፡፡ ወንዙን ከተሻገሩ በኋላም ኤልያስ ደቀ መዝሙሩ ኤልሳዕን “ከአንተ ሳልወሰድ ላደርግልህ የምትፈልገውን ለምነኝ፤” አለው፡፡ ኤልሳዕም “በአንተ ላይ ያደረው መንፈስ ቅዱስ እጥፍ ኾኖ በእኔ ላይ እንዲያድር ይኹን፤” ብሎ መለሰ፡፡ ኤልያስም “ዕፁብ ነገርን ለመንኸኝ፡፡ ነገር ግን እኔ ከአንተ ተለይቼ በማርግበት ጊዜ ካየኸኝ እንዳልኸው ይደረግልሃል፡፡ በማርግበት ሰዓት ካላየኸኝ ግን አይደረግልህም፤” አለው፡፡

ሁለቱም እየተነጋገሩ ሲሔዱ የእሳት ሠረገላ፣ የእሳት ፈረስ በመካከላቸው ገባና ለያያቸው፡፡ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ፣ በንውጽውጽታ፣ በእሳት ሠረገላ ዐረገ፡፡ ኤልሳዕም የኤልያስን ወደ ሰማይ መወሰድ አይቶ ጮኸ፤ “የእስራኤል ኃይላቸው፣ ጽንዓታቸው አባ፣ አባት ሆይ” አለ፡፡ ከዚያ በኋላ ዳግመኛ አላየውም፡፡ ኤልያስም ልብሱን ከሁለት ከፈለው፡፡ መጠምጠሚያውንም ለኤልሳዕ ጣለለት፡፡ የኤልያስ ጸጋና በረከትም በኤልሳዕ ላይ አደረ፡፡

ይህም ምሳሌ ነው፤ ኤልያስ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግሮ ወደ ብሔረ ሕያዋን እንደ ገባ ዅሉ፣ ከውኀና ከመንፈስ ቅዱስ የሚወለዱ ምእመናንም የእግዚአብሔርን መንግሥት ይወርሳሉ፡፡ “ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማየት አይችልም፤” እንዳለ ጌታችን በወንጌል /ዮሐ.፫፥፫/፡፡

ነቢዩ ኤልያስ በዘመነ ኦሪት ከነበሩት ዐሥራ አምስቱ ነቢያት (ሙሴ፣ ኢያሱ፣ ሳሙኤል፣ ዮናታን፣ ጋድ፣ ዳዊት፣ ሰሎሞን፣ ኤልሳዕ፣ ዕዝራ፣ ኢሳይያስ፣ ዳንኤል፣ ኤርምያስ፣ ሕዝቅኤል እና መጥምቁ ዮሐንስ) መካከል አንደኛው ነቢይ ነው፡፡ ይህ ቅዱስ በአካለ ሥጋ ከጌታችን ጋር በደብረ ታቦር የተነጋገረ ነቢይ፤ የጣዖታትን መሥዋዕት አፈራርሶ ለልዑል እግዚአብሔር እውነተኛ መሥዋዕትን ያሳረገ ካህን፤ ሥርዓተ ምንኵስናን የጀመረ ባሕታዊ፤ ስለ እግዚአብሔር ለፍርድ መምጣት አስቀድሞ የሚሰብክ ሐዋርያ ነው /የገድለ ኤልያስ ነቢይ መቅድም፣ ቍ.፩-፮/፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስን ታላቅነት ሲመሰክር ዮሐንስን “ኤልያስ” ብሎታል፡፡ ዮሐንስ ልብሱ የግመል ፀጉር እንደ ኾነ ዅሉ፣ ኤልያስም ፀጕራም መኾኑ፤ ሁለቱም መናንያን፣ ጸዋምያን፣ ተሐራምያን /ፈቃደ ሥጋን የተዉ/፣ ዝጉሐውያን /የሥጋን ስሜት የዘጉ/፣ ባሕታውያን መኾናቸው፤ በተጨማሪም ዮሐንስ ሄሮድስና ሄሮድያዳን እንደ ገሠፃቸው ዅሉ፣ ኤልያስም አክአብና ኤልዛቤልን መገሠፁ፤ ዮሐንስ ከክርስቶስ ቀዳሚ ምጽአት /በአካለ በሥጋ መገለጥ/ አስቀድሞ እንዳስተማረ ዅሉ፣ ኤልያስም ከክርስቶስ ዳግም ምጽአት አስቀድሞ የሚያስተምር መኾኑ ያመሳስላቸዋልና ጌታችን ዮሐንስን ‹ኤልያስ› ብሎ ጠርቶታል /ትርጓሜ ወንጌል፣ ማቴ.፲፩፥፲፬፤ ፲፯፥፲-፲፫/፡፡

መምህራነ ቤተ ክርስቲያን እንዳስተማሩን ነቢዩ ኤልያስ ከጌታችን ዳግም ምጽአት አስቀድሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለዓለም በመስበክ በሰማዕትነት ይሞታል፡፡ አንዳንዶቹ ይህንን ትምህርት ይዘው “ኤልያስ መጥቷል” እያሉ ምእመናንን ያሰናክላሉ፤ ነቢዩ እነርሱ እንደሚሉት በስውር ሳይኾን ዓለም እያየው በግልጽ እንደሚመጣ ስለምናምን ኤልያስ ወደዚህ ምድር የሚመጣው የምጽአት ቀን ሲቃረብ መኾኑን አስረግጠን እንናገራለን፡፡

በመጨረሻም ዅላችንም እንደ ነቢዩ ኤልያስ በአካለ ሥጋ ሳይኾን በክብር ከፍ ከፍ እንል ዘንድ በሕሊና ልናርግ ማለትም በመልካም ምግባር ልንጐለምስ ያስፈልጋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ እንደ ነቢዩ ኤልሳዕ የአባቶቻችን ጸጋ በላያችን ላይ ያድርብን ዘንድ ከቅዱሳን እግር ሥር እና ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቅፅር፤ እንደዚሁም ከተዋሕዶ ሃይማኖታችን አስተምህሮ መውጣት የለብንም፡፡

ምንጭ፡–

  • መጽሐፈ ስንክሳር፣ ታኅሣሥ እና ጥር ቀን የሚነበብ፡፡
  • የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ ኢ.መ.ቅ.ማ፤ 2002 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፤ ገጽ 173፡፡
  • ገድለ ኤልያስ ነቢይ፣ መ/ር ተስፋ ሚካኤል ታከለ፤ ፳፻፭ ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፡፡

One Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *